አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከሰብዓዊ ባህሪያት አንዱ የሆነው አዎንታዊ የውድድር መንፈስ መኖር ጤናማ ቢሆንም በአንጻሩ ሲሆን ደግሞ ከፍተኛ የሥነ-ልቦና ችግር እንደሚሆን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የሥነ-ልቦና ባለሙያው አትክልት ዳኘው ራስን ያለመቀበል የሚፈጥረውን ያልተገባ የውድድር መንፈስ አስመልክተው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
በቆይታቸውም ፥ ከሰብዓዊ ባህሪያት አንዱ የሆነው አዎንታዊ የውድድር መንፈስ መኖር ጤናማ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ያልተገባ ውድድር ሰዎች ጠቃሚ ያልሆነ፣ የማይገባቸውንና አላስፈላጊ የሆነ ውድድር ውስጥ መግባታቸው ራሳቸውን ያለመቀበልና ራስን ያለመሆን እንደሆነም ነው የሚገልጹት፡፡
በዚህ የሚፈጠር ያልተገባ የውድድር መንፈስ ውስጥ መግባት ደግሞ በእርስ በርስ ግንኙነቶች ላይ ከሚፈጥረው አሉታዊ ጫና ባሻገር ራስን እስካለመሆንና ራስን አለመቀበል እውነታ ውስጥ ይመለከታል ይላሉ ባለሙያው፡፡
በዚህ ያልተገባ የውድድር ሒደት ውስጥ ሰዎች ቀደም ካለው ጸባያቸው ያፈነገጠና ሐሰተኛ ማንነትን ሊያዳብሩ እንደሚችሉም አብራርተዋል፡፡
ሰዎች ወዳልተገባ ውድድር እንዲገቡ የሚያደርጉ የተለያዩ ምክንያቶችን የሥነ-ልቦና ባለሙያው ያነሳሉ ፡-
• ራስን አለመቀበል፡- ያለፉበትን ነገር ያለቅድመ ሁኔታ ለመቀበል አለመቻል ፣ • ማህበራዊ ጫና፡- ማህበራሰቡ (ቤተሰብ፣ ጓደኛ ወዘተ) እንዲሆኑ የሚፈልገው ወይም የሚጠብቀውን ነገር ከራስ በላይ ማድረግ • የአቻ ግፊት
• የራስን አቅም አለማወቅና ውስጣዊ እምቅ ሃብቶችን አለመረዳት • አስተዳደግ • በቂ ክህሎት አለማዳበር
ራሰዎን ካልተቀበሉ ሌሎች ሰዎች እርስዎን ለመቀበል ይቸገራሉ፤ ስለዚህም እያንዳንዱ ሰው ራሱን መቀበል እንደለበትም የሥነ-ልቦና ባለሙያው ይመክራሉ፡፡
በዚህም ከራስ አልፎ ሰዎች ማንነታችንን እንዲቀበሉን እንደሚረዳም ነው ያብራሩት፡፡
ራስን ለመረዳት የሚሰጡ ጥሞናዎች ሃሰተኛ ማንነትን ከመገንባትና ያልተገባ የውድድር መንፈስ እንዲላቀቁ አጋዥ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም የሕይዎት ክህሎት ስልጠናዎች፣ ራስን መመልከት(መገምገም)፣ የሌሎችን ቀና አስተያየት በመውሰድ ራስን መፈተሽም ካልተገባ ውድድር እንዲላቀቁ እንደሚያግዝም ነው የሚያስረዱት፡፡
ጉዳዩ ከፍ ካለ እና አሳሳቢ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ የሥነ-ልቦና ድጋፍ ማግኘት እንደሚገባ የሥነ-ልቦና ባለሙያው መክረዋል፡፡