የሀገር ውስጥ ዜና

የሰራዊት ቀን በዓልን አስመልክቶ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

October 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢፌዴሪ መከላከያ ጠቅላይ መምሪያ የ116ኛ የሰራዊት ቀን በዓልን አስመልክቶ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በፓናል ውይይቱ ላይ ጄኔራል ጌታቸው ጉዲና÷ ኢትዮጵያ ለረጅም ዘመናት በተለያዩ የታሪክ ሂደቶች እያለፈች ለዛሬ ስትደርስ ወታደራዊ ታሪኳ የጎላ ስፍራ ይይዛል ብለዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያን ሀገረ-መንግስት በማጽናት ረገድም በተለያዩ ወቅቶች የሠራዊቱ ተጋድሎና መስዋዕትነት እንደማይዘጋ ተናግረዋል።

የመከላከያ ሰራዊታት ሀገራዊ ደህንነትን ከየትኛውም አደጋ እየተከላከለና መስዋዕትነት እየከፈለ ሀገር በማስቀጠል ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው÷በፓናል ውይይቱም የሠራዊቱን ሀገር የማጽናት ብቃት የሚያጎለብቱ ቁም-ነገሮች የሚገኙበት እንደሚሆን አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጠንካራ እና አስተማማኝ የብቃት ደረጃ ላይ ይገኛልም ነው ያሉት፡፡

በፓናል ውይይቱ የመከላከያ አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር ተወካዮች፣የቀድሞ የኢትዮጵያ ሰራዊት አመራሮችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸውን የመከላከያ ሰራት መረጃ ያመላክታል፡፡

116ኛ የሰራዊት ቀን ጥቅምት 15 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በልዩ ልዩ ክንውኖች እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡