የሀገር ውስጥ ዜና

በጋምቤላ ክልል የትምህርት ዘርፍ ችግሮችን ለመቅረፍ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ተጠየቀ

By Shambel Mihret

October 24, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 13፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል በትምህርት ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ጥሪ አቅርቧል።

በመማር ማስተማር ሥራውና በዘርፉ በሚታዩ ችግሮች ዙሪያ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የውይይት መድረክና የመስክ ምልከታ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጄት በውይይቱ ወቅት÷ በትምህርት ጥራት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊሠሩ ይገባል ብለዋል።

የጋምቤላ ከተማ ከንቲባ አቶ ጋትሉዋክ ጋች በበኩላቸው÷ ከተማ አስተዳደሩ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በመድረኩ በጋምቤላ ከተማ የሚገኙ የትምህርት አመራሮች፣ ርዕሣነ መምህራን፣ ወላጆችና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት መሳተፋቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡

እንዲሁም የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት የጋምቤላ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን፣ ራስ ጎበና እና ዊቡር አንደኛና ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት ቤቶችን ጎብኝተዋል።