አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ነጻ፣ ገለልተኛ፣ ዘመናዊና ወገንተኝነቱ ለሕገ መንግስቱ የሆነ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባት ወሳኝ መሆኑን የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
አቶ አደም ፋራህ 116ኛውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ቀን አስመልክተው የ’እንኳን አደረሳችሁ’ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በመልዕክታቸውም÷ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ኢትዮጵያን ለማፅናትና ሕዝብን ለመጠበቅ ከሁሉም ነገር በላይ ውድ የሆነውን ህይወቱን የሚሰጥ የሕዝባዊነት፣ የአርበኝነትና የብሔራያዊነት መገለጫ ነው ብለዋል፡፡
ከሀገር መከላከያ ጎን መቆም ማለት ለሀገር ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መከበር የዜግነት ግዴታን መወጣት እንዲሁም ለሕዝብ ክብርና ጥቅም መቆም ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡
በአንጻሩ የሀገር መከላከያን ማጥቃት ማለት ኢትዮጵያን ማጥቃትና ሕዝብን መጉዳት እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
ለጠንካራ ሀገረ መንግስት ግንባታ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ዘመናዊና ወገንተኝነቱ ለሕገ መንግስቱ የሆነ የሀገር መከላከያ ሠራዊት መገንባት ወሳኝ መሆኑንም አጽንኦተ ሰጥተዋል፡፡
ከዚህ አንፃር ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተጀመረውና ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበ ያለው ጥረት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም ሠራዊቱ ለከፈለውና እየከፈለ ላለው የላቀ መስዋዕትነት ተገቢውን እውቅናና ክብር መስጠት እንደሚገባ መናገራቸውን የፓርቲው መረጃ ያመላክታል፡፡