አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እምቅ ፀጋ እና የሰው ሀይል ያለው ክልል ነው ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሳው ተናገሩ፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ከማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጋር በመተባበር ያዘጋጀው “መደመር ሀብት ለመፍጠር፣ ፀጋን ለማስተዳደር አርበኝነትን ለማሻገር” በሚል መሪ ሀሳብ ውይይት እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ስራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ፥ ኢዜአ የመደመር እሳቤን ለማስረፅ “የመደመር ጉዞ” በሚል ማዕቀፍ በተለያዩ የሃገሪቱ ከተሞች የፓናል ውይይቶችን እያካሄደ መሆኑን ገልፀዋል።
የመድረኩ ዋነኛ ዓላማም በመደመር እሳቤ ላይ ሰፊ ግንዛቤ በመፍጠር ብሄራዊ መግባባት፣ አንድነትና አብሮነትን ማጠናከር ነው ብለዋል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንደሻው ጣሰው በበኩላቸው ÷አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እምቅ ፀጋ፣ የሰው ሀይል እና ተወራራሽ ባህሎች ባለቤት መሆኑን አንስተዋል።
የመደመር የፓናል ውይይት መዘጋጀቱ ክልሉን በማስተዋወቅ ከሌሎች እህት ወንድም ህዝቦች ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በቅንጅት መስራት የመደመር ጉዞን ለማሳካት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
በመድረኩ ላይ የፌዴራል መንግስት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት እና ሌሎች እንግዶች እየተሳተፉ ነው።
በሳሙኤል ወርቃየሁ