የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው – አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ

By Shambel Mihret

October 25, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 14፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ ገለጹ።

የቼክ ሪፐብሊክ የልማት ትብብር የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልን በተመለከተ ከተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ካልሆነ ተቋማት ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።

በመድረኩ በኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሴክ÷ የአየር ንብረት ለውጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ፈተና ሆኖ መቀጠሉን ገልጸዋል።

በአፍሪካ ተጽዕኖው ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው÷ ለድርቅ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንሸራተትና ለሌሎች ተያያዥ ችግሮች ማጋለጡንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለአካባቢ ጥበቃ የሰጠችው ትኩረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፤ ችግሩን ለመከላለክና ለውጥ ለማምጣት የሀገራትትብብር አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ኢንስቲትዩት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዳንኤል ጎቦናያ÷ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የጋራ ምላሽ ይፈልጋል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

በመድረኩ ቼክ ሪፐብሊክ በኢትዮጵያ የአየር ንብረት ተጽዕኖ መቋቋም የሚያስችል የግብርና ልማት እንዲስፋፋና የአረንጓዴ ልማት እንዲጠናከር እየሰራች መሆኑ ተመላክቷል።