ዓለምአቀፋዊ ዜና

አሜሪካ በተመረጡ የሶሪያ ግዛቶች ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተሰማ

By Melaku Gedif

October 27, 2023

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 16፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአሜሪካ ጦር በምስራቅ ሶሪያ በተመረጡ ቦታዎች ላይ ወታደራዊ ጥቃት መፈጸሙ ተሰምቷል፡፡

ጥቃቱ ኢራን እና በእርሷ የሚደገፉ ታጣቂዎች የሚጠቀሙባቸውን ወታደራዊ ማዕከላት ኢላማ ያደረገ መሆኑን የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በምሥራቅ ሶሪያ ሁለት ቦታዎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት በሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቀጥተኛ ትዕዛዝ የተፈጸመ መሆኑ ተነግሯል፡፡

የተፈጸመው ጥቃት በቅርቡ በኢራቅ እና ሶሪያ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሠፈሮች ላይ ለተፈጸመ ጥቃት አጸፋዊ ምላሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ጥቃቱ በእስራኤል እና ሃማሰ መካከል እየተካሄደ ካለው ጦርነት ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ሚኒስቴሩ መግለጹን አር ቲ ዘግቧል፡፡