ስፓርት

ሱፐር ሰንዴይ ማንቹሪያን ደርቢ በኦልድትራፎርድ

By Mikias Ayele

October 29, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 18፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ10ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ማንቼስተር ዩናይትድ ከማንቼስተር ሲቲ የሚያደርጉት የማንቹሪያ ደርቢ ጨዋታ ተጠባቂ ነው፡፡

ምሽት 12:30 ላይ በሚደረገው ጨዋታ ማንቼስተር ሲቲ ከመሪው ቶተንሃም ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማጥበብ ወደ ሜዳ የሚገባ ሲሆን ማንቼስተር ዩናትድ ባንፃሩ የደርቢ ክብሩን ለማስጠበቅ እና ካለበት የውጤት ቀውስ ለማገገም ወደ ሜዳ ይገባል፡፡

በማንቼስተር ዩናይትድ በኩል አሮን ዋን ቢሳካ ከጉዳት መልስ እንደሚሰልፍ የተገለጸ ሲሆን የመሃል ሜዳ ሞተሩ ካስሜሮ የመሰለፉ ጉዳይ አጠራጣሪ ሆኗል፡፡

በማንቼሰተር ሲቲ በኩል ኬቨን ዲቡረይና በጉዳት ማኑኤል አካንጂ ደግሞ በቅጣት የማይሰለፉ ሲሆን እነሱን በመተካት ጆን ስቶንስ እና በርናርዶ ሲልቫ ወደ ሜዳ ይገባሉ፡፡

የማንቼስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ÷ የማንቼስተር ደርቢ ከነጥብ በላይ ነው፣ ጨዋታውን ለማሸነፍ ሁሉንም አይነት አማራጭ እንጠቀማለን ብለዋል፡፡

የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጋርዲዮላ በበኩላቸው÷ በኦልትራፎርድ መጫወት ሁሌም ለየት ያለ ስሜት እንደሚኖረው ጠቅሰው፤ ተጫዋቾቻቸው እና የቡድን አመራሮቻቸው በጥሩ ስነ ልቦና እና ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

በጨዋታው መጀመሪያ በቅርቡ ህይዎታቸው ያለፈው የቀድሞው የማንቼስተር ዩናይትድ ተጫዋች ሰር ቦቢ ቻርልተን የህሊና ፀሎት እንደሚደረግለት ስካይ ስፖርት አስነብቧል፡፡