አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኦሮሚያ ክልል የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎች በልዩ ትኩረት እንደሚሰሩ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ሃላፊ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ÷የክልሉን የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ግምገማን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም÷ በሩብ ዓመቱ ከታዩ ስኬቶች መካከል ከክልል እስከ ቀበሌ ድረስ ያለው አመራር የተግባር አንድነት ማሳየቱ፣ የወጡ ዕቅዶች ህዝቡ ጋር እንዲደርሱ እና ህዝቡ እንዲወያይበት መደረጉ እንዲሁም ስራዎችን አስተባብሮ ለመስራት የተደረጉ ጥረቶች ይጠቀሳሉ ብለዋል።
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች፣ በክልሉ የወጡ ኢኒሼቲቮችን ከዳር ለማድረስ የተደረጉ ጥረቶች ሌላኛው በስኬት የታዩ መሆናቸውንም አንስተዋል።
በግምገማው እንደውስንነት ከተነሱት መካከልም ዕቅዱን ለማሳካት የቁርጠኝነት ችግሮች መስተዋላቸው፣ በሚፈለገው ደረጃ ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት ያለማድረግ እንዲሁም አልፎ አልፎ ህዝብን ከማገልገል አንጻር ውስንነት መስተዋላቸውን ገልጸዋል።
የታዩ ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እንዲሁም ውስንነቶችን ለመቅረፍ በማለም በልዩ ትኩረት ሊሰሩ የሚገባቸው ነጥቦች መቀመጣቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የክልሉ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ባለፉት ሶስት ቀናት በአዳማ መካሄዱ ተገልጿል።