የሀገር ውስጥ ዜና

በሆልቲካልቸር ዘርፍ 741 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ ነው

By ዮሐንስ ደርበው

October 30, 2023

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 19 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2016 ዓ.ም በሆልቲካልቸር ዘርፍ 741 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ገቢ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የግብርና ሚኒስቴር በሆልቲካልቸር ዘርፍ ላይ ያሉ መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ውይይት ከባለድርሻ አካላት ጋር እያደረገ ይገኛል።

በውይይቱ ላይ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፥ የሆልቲካልቸር ኢንቨስትመንት የሥርዓተ ምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል።

ዘርፉ የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግርን በመፍታትና የስራ ዕድል በመፍጠር የማይተካ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ተናግረዋል።

ከ18 ዓመት በፊት ሙሉ ለሙሉ በውጭ ሀገራት ባለሙያዎች ይመራ የነበረውን ይህን ዘርፍ የክህሎት ሽግግር በማድረግ አሁን ላይ 98 በመቶውን በኢትዮጵያውያን እንዲመራ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ በዓለም አቀፍ እና ሀገራዊ ምክንያቶች ዘርፉን እየፈተኑ የሚገኙ ችግሮች እንዳሉም አንስተዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በውይይት ተግባራዊ ስራ ከተሰራ የታቀደውን 741 ነጥብ 8 ሚሊየን ዶላር ገቢ ማሳካት እንደሚቻልም አስረድተዋል።

በዘመን በየነ