የሀገር ውስጥ ዜና

አቶ ርስቱ ይርዳው ለፊቼ ጨምበላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

By Tibebu Kebede

May 20, 2020

አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው ለሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጨምበላላ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም የሲዳማ ብሄር የዘመን መለወጫ በዓል ፊቼ ጨምበላላ ለረጅም አመታት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የቆየ የማንነታችን መገለጫ ከመሆን ባለፈ ለሀገራችን እና ለመላው የዓለማችን ህዝቦች ሀብት መሆኑ እሙን ነው ብለዋል።

በዓሉ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከማይዳሰሱ የሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት ተመዝግቦ እውቅና የተሰጠው ሲሆን በየአመቱ በታላቅ ድምቀት እየተከበረ ቆይቷልም ነው ያሉት።

በዓሉን አስመልክቶ ወደ ኢትዮጵያ ለሚመጡ ጎብኚዎች የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ አንጻር ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑንም አንስተዋል።

ፊቼ ጨምበላላ ኢትዮጵያን ከሌሎች ዓለማት ጋር ለማስተዋወቅ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ ርስቱ፥ ይህንን ታላቅ የማንነታችን እሴት መገለጫ የሆነውን በዓል ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ጠብቀው ለዘመናት ላቆዩልን የሲዳማ አባቶች እና እናቶች ላቅ ያለ ምስጋናና አክብሮት አለኝ ብለዋል።

ይህንን ቱባ በዓል ጠብቆ በማቆየት ረገድ የወጣቶች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት ድርሻም ጉልህ መሆኑን አቶ ርስቱ ጠቁመዋል።

በፊቼ ጨምበላላ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነት እና መቻቻል ጎልቶ የሚታይበት በዓል በመሆኑ በዚህ ወቅት ከምንም በላይ እነዚህ እሴቶች እንደሚያስፈልጉም አውስተዋል።

“በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የዘንድሮውን የፊቼ ጨምበላላ በዓል በአደባባይ ማክበር ባንችልም የገጠመንን ፈተና በጽናት ለማለፍ ሁላችንም ጥንቃቄ በማድረግ የራሳችንን እና የምንወዳቸውን ሰዎች ህይወት መታደግ ይገባናል” ብለዋል አቶ ርስቱ።

“ቫይረሱን በአግባቡ ተቆጣጥረን መጭውን የፊቼ ጨምበላላ በዓል ለማክበር የምንበቃበት ጊዜ እውን እንደሚሆን ያለኝን ተስፋ እገልጻለሁ” ነው ያሉት በመልዕክታቸው።

መረጃው የደቡብ ክልል ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ነው

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።