ጤና

ስለ ሀሞት ጠጠር አጋላጭ ምክንያቶች ምን ያህል ያውቃሉ?

By Feven Bishaw

October 30, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሐሞት ከረጢት/ፊኛ ጠጠር በተለምዶም የሐሞት ጠጠር የሚባለው የሐሞት ፊኛ ውስጥ ጠጠር ሲከማች ነው።

ይህ ጠጠር ለምን እና እንዴት እንደሚፈጠር ሳይንሳዊ ድምዳሜ ላይ መድረስ ባይቻልም የተለያዩ መላምቶችን ግን መጥቀስ ተችሏል።

እነዚህም መላምቶች፣ የኮሌስትሮል በሐሞት ውስጥ መብዛት፣ ቢሉሩቢን (መወገድ ሲገባቸው ያልተወገዱ የቀይ የደም ህዋሳት) በሐሞት ውስጥ መብዛትና የሐሞት ፊኛ በውስጡ የሚገኘውን የሐሞት ፈሳሽ ወደ አንጀት መግፋት አለመቻል የሚሉትን ያጠቃልላሉ።

የሐሞት ጠጠር አጋላጭ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ጾታ (በአብዛኛው ሴቶች ተጋላጭ ናቸው)፣ ዕድሜ ከ40 አመትና ከዚያ በላይ መሆን፣ የሰውነት ክብደት መጨመር፣ የሌሎች ተጓዳኝ በሽታ (እንደ ስኳር፣ ደም ግፊት) መኖር፣ የተለያዩ መድሀኒቶች፦ የሚዋጥ የወሊድ መቆጣጠርያ፣ ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ መድሀኒቶች እና ቤተሰብ ውስጥ የሐሞት ጠጠር ያለበት ሰው መኖር ከብዙዎቹ ዋናዎቹ ናቸው።

የሐሞት ከረጢት ጠጠር ምን አይነት ምልክቶች አሉት?

አብዛኛውን ጊዜ ምንም አይነት ምልክት አያሳይም፤ ስለሆነም የሚታወቀው ለሌላ በሽታ ምርመራ በሚደረግበት ወቅት መሆኑን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል።

ምልክት ካሳየ ግን ዋነኛ የሚሆነው የሆድ ህመም ሲሆን ህመሙም የመውጋት ስሜት ይኖረዋል፤ በተጨማሪም ማስታወክ፣ ማቅለሽለሽ እና ትኩሳት እንደ ምልክቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ።

የሐሞት ጠጠር ሕክምናው ምንድነው?

ምልክት ካላሳየ ቋሚ ክትትል ከማድረግ ውጪ ሌላ ህክምና የለውም፤ ምልክት ካሳየ ግን የቀዶ ሕክምና ብቸኛው መፍትሔ ነው።