የሀገር ውስጥ ዜና

ኡስታዝ አቡበከርን በማገት መኪናውን ሊነጥቁ ነበር ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የቀረበው ዝርዝር ክስ በንባብ ተሰማ

By Feven Bishaw

October 31, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን የተባለውን ግለሰብ በማገት መኪናውን ሊነጥቁ ነበር ተብለው በተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ የቀረበው ዝርዝር ክስ በንባብ ተሰማ።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በሰባት ተከሳሾች ላይ ባለፈው አርብ የወንጀል የተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ አቅርቦባቸው ነበር።

በአጠቃላይ ክሱ የቀረበባቸው ተከሳሾች 1ኛ የሁለተኛ ተከሳሽ ወኪል የሆነው ፍፁም ተክሉ አፅብሀ፣2ኛ የኡስታዝ አቡበከር ሁሴንን ተሽከርካሪ በስሙ አዙሯል የተባለው አበራ ነጋሳ ሆርዶፋ፣ 3ኛ በአዲስ አበባ አሸከርካሪ ተሸከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት ውስጥ የተሽከርካሪ አገልግሎት ባለሙያ ናቸው የተባሉት አብዮት አበራ፣ 4ኛ ልየው አሰፋ አንዱአለም፣ 5ኛ አለሙ ኦልጅራ እንዲሁም 6ኛ የአ/አ ፖሊስ ኮሚሽን የንፋስ ስልክ ፖሊስ መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቡድን ኃላፊ ዋና ሳጅን መኳንንት ተመስገን እና 7ኛ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ቡድን አባል የሆነው ዋና ሳጅን ገመቹ ብርሃኑ ናቸው።

ከተከሳሾቹ መካከል በተለይም ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር ያሉ ተከሳሾች በፌደራል ፖሊስና በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ክትትል በቁጥጥር ስር ውለው በሙስና ዘርፍ ዐቃቤ ሕግ መሪነት የምርመራ ማጣሪያ ሲደረግባቸው እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

በተከሳሾቹ ላይ የቀረበው ክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው 1ኛ ተከሳሽ የ2ኛ ተከሳሽ ወኪል በመሆን ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር የሆነውንና ከላይ የተጠቀሰውን ተሽከርካሪ አስቀድመው የተሽከርካሪውን መረጃ ለማግኘት ከ3ኛ፣ 4ኛ እና 5ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር “ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ” በሚል በግል ተበዳይ ስም ተመሳስሎ ከለሚ ኩራ ክ/ከ/ወ/10 የሲቪል ምዝገባና ነዋሪዎች አገልግሎት ቅ/ፅ/ቤት እንደተሰጠ በማስመሰል በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ እና ያላገባ የምስክር ወረቀት ተጠቅመዋል የሚል ዝርዝር ይገኝበታል።

በዚህ መልኩ በተዘጋጀ ሀሰተኛ የነዋሪነት መታወቂያ በመጠቀም በነሃሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ሙሴ መረሳ ኃይሉ ለሚባል ግለሰብ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን ነኝ በሚል በሀሰት ውክልና መሰጠቱን ዐቃቤ ሕግ በክሱ ገልጿል።

በዚሁ ውክልና ስልጣን መሰረት ደግሞ ነሃሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በእጃቸው በሌለ ተሸከርካሪ የሽያጭ ውል እንዲፈፀም ካደረጉ በኋላ በ5ኛ ተከሳሽ አማካኝነት በህገወጥ መልኩ ሊብሬ በማሰራት ንብረትነቱን ወደ 2ኛ ተከሳሽ እንዲዞር ማድረጋቸውም በክስ ዝርዝሩ ተመላክቷል።

ከዚህ በኋላ ደግሞ 1ኛ ተከሳሽ መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም የግል ተበዳይ ኡስታዝ አበቡከር ተሽርካሪውን እየነዳ ባለበት ወቅት ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የድንገተኛ ስልክ ጥሪ ማዕከል 991 በመደወል መኪናው እንደተሰረቀበትና በመንገድ ላይ እየተነዳ እንዳየው በመግለፅ እንዲያዝለት በማመልከት የፌዴራል ፖሊስ ኢንተለጀንስ ሰራተኛ ከሆነው 7ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን መኪናውን አስቁመውና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ ቁጥጥር ስራ በሚሰሩት የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በሆኑት አካላት አማካኝነት ተሽከርካሪው እንዲያዝ በማድረግና በሀሰት ተሽከርካሪው ከዚህ በፊት የጠፋባቸው መሆኑን በመግለፅ ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ለቡ ፖሊስ ጣቢያ በማመልከት ተሸከርካሪውን ሊወስዱ ሲሉ የተያዙ መሆኑ በክሱ ተገልጿል።

3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ ከተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት ውጭ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር የግል ተበዳይን ተሽከርካሪ ነሃሴ 6 ቀን 2014 ዓ.ም አስቀድሞ የዋጋ ግምት እንዲፃፍ በማድረግና ሽያጭ ተፈፅሟል በሚል ከ4ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ባለቤትነቱን ከግል ተበዳይ ከኡስታዝ አቡበከር ስም ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ካደረገ በኋላ የግል ተበዳዩ በ2015 ዓ.ም ዓመታዊ የተሽከርካሪ ቦሎ እድሳት ለማድረግ ወደ ተቋሙ በሄደበት ወቅት በህገወጥ የስም ዝውውር መደረጉንና ሀሰተኛ የተሽከርካሪው ሊብሬ በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዳለ እያወቀ ለግል ተበዳዩ ቦሎውን ያደሰለት መሆኑ በክሱ ሰፍሯል።

በዚሁ መልኩ 4ኛ ተከሳሽ ደግሞ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሸከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት የዳታ ኢንኮደር ባለሙያ በመሆን ሲሰራ በስራ ሰነድ ማጣራትና ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ እያለበት ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ የባለቤትነት ስም መረጃውን ሳያጣራ እና ሳያረጋግጥ በሲስተም ላይ ከ3ኛ ተከሳሽ ጋር በመመሳጠር ወደ 2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲዞር ማድረጉ በክሱ ተመላክቷል።

5ኛ ተከሳሽን በሚመለከት ደግሞ የአዲስ አበባ አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን የአዲስ ከተማ ቅ/ፅ/ቤት የተሸከርካሪ ፈቃድ አገልግሎት ባለሙያ በመሆን በማገልገል ላይ እያለ በስሙ ከንብረት ክፍል በወጣ ሊብሬ ሲስተም ላይ ሳይመዘገብ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ የሆነውን ተሽከርካሪ ባለቤትነት በ2ኛ ተከሳሽ ስም እንዲሆን ማድረጉ በክስ ዝርዝሩ ሰፍሯል።

6ኛ ተከሳሽ በሚመለከት ተከሳሹ የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ/ፖ/መምሪያ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ቲም ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ሳለ ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር የሆነውን ተሽከርካሪ መረጃ በሚመለከት በህግ ከተሰጠው ኃላፊነት ውጭ ምንም አይነት የወንጀል ጥቆማና አቤቱታ ባልቀረበበት እና የምርመራ ስራ ባልተጀመረበት ጉዳይ ላይ የተሽከርካሪው መረጃ እንዲላክለት ለአዲስ ከተማ ክ/ከ/መንገድ ትራንስፖርት በቀን ነሃሴ 3 ቀን 2015 ዓ.ም ደብዳቤ በመፃፍ ማህደር ኮፒው እንዲመጣ በማድረግ ለ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች አሳልፎ የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል።

በተጨማሪም በክሱ ላይ እንደሰፈረው 7ኛ ተከሳሽ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የኢንተለጀንስ ሰራተኛ ሆኖ ሲያገለግል የተሰጠውን ተግባርና ኃላፊነት ያለአግባብ በመጠቀም ከ1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር መስከረም 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከተቋሙ ምንም አይነት የሥራ ስምሪት ሳይሰጠው የግል ተበዳይ ተሸከርካሪው ላይ እንዳለ በኮ/ቀ/ክ/ከ/ወ/01 ልዩ ቦታው ሳሚ ካፌ አካባቢ ሲደርስ በማስቆም እና ወደ ፖሊስ ጣቢያ በመውሰድ እንዲታሰር ማድረጉም ተጠቅሷል።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ ንብረትነቱ የግል ተበዳይ ኡስታዝ አቡበከር ሁሴን መሀመድ የሆነውንና የዋጋ ግምቱ 7 ሚሊየን ብር የሆነ ቪ8 ተሽከርካሪ ሀሰተኛ ሰነዶችን በመጠቀም፣ ማህደሩን በመለወጥና በሽያጭ በማስተላለፍ ለመውሰድ ሲሉ የተያዙ መሆኑ ተጠቅሶ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ነው የቀረበባቸው።

በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ዛሬ በነበረው ቀጠሮ ከ1ኛ እስከ 5ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱ ተከሳሾች ችሎት ቀርበው የክስ ዝርዝሩ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ ክሱ በንባብ ተሰምቷል።

ተከሳሾቹ በክሱ ላይ የክስ መቃወሚያ ካላቸው ለመጠባበቅ ለህዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ