አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል ሰላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ ማህበረሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ በማጠናከር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል።
የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር ነስሪ ዘካሪያ÷ በክልሉ በ2015 በተከናወኑ ተግባራት እንዲሁም በ2016 ሊከናወኑ በታቀዱ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ኮሚሽነሩ በመግለጫቸው÷ በ2015 በጀት ዓመት በተከናወኑ በተለያዩ ስራዎች የክልሉን አንፃራዊ ሰላም ማስቀጠል ተችሏል ብለዋል።
በ2016 በጀት ዓመትም ህብረተሰቡን በማሳተፍ በክልሉ ሰላምና የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተለያዩ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የተቋሙ የወንጀል መከላከል አቅምን በቴክኖሎጂ የመደገፍ እንዲሁም የፖሊስ የወንጀል መከላከል ተግባርን በተለያየ የስራ ዘርፎች የማዋቀር እንዲሁም ድንገተኛ የወንጀል ክስተቶች ሲያጋጥሙም ውጤታማ የምርመራ ሂደቱን ለማካሄድ የሚያስችሉ ስራዎች ይከናወናሉ ብለዋል፡፡
የማህበረሰቡን የወንጀል መከላከል ግንዛቤ ለማሳደግ ስልጠናዎች በመስጠት በክልሉ በሚገኙ 36 ቀበሌዎች የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን ለማሳደግ እንደሚሰራ ገልጸው፤ ህብረተሰቡ ቀጣይነት ያለው ሰላም ለማስፈን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
በትራፊክ አደጋ የሚደርሱ ጉዳቶችን ለመቀነስም የትራፊክ ቁጥጥር አቅምን በማሳደግ በትራፊክ የሚጣሱ ደንቦች እንዲቀንሱ እና ሕግ የማስከበር ስራዎች እንደሚከናወኑ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
የእሳት አደጋ ክስተትን በአፋጣኝ ለመመከት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በማጠናከር የእሳት አደጋን የመከላከል አቅምን ለማሳደግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡