የሀገር ውስጥ ዜና

አፍሪካ በምግብ ምርት ራሷን እንድትችል መሪዎቿ ቆርጠን ተነስተናል – ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ

By Meseret Awoke

October 31, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 20፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) አፍሪካ በምግብ ምርት ራሷን እንድትችል መሪዎቿ ቆርጠን ተነስተናል ሲሉ የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ሣኅለወርቅ ዘውዴ ገለጹ፡፡

ፕሬዚዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትና ጉዞ ላይ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊ አኪንዉሚ አድሲና ጋር ቦርላግ በተባለ የውይይት መድረክ ላይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም፥ ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናዋን ለማረጋገጥ እየተጓዘች ስላለው አስደናቂ ጉዞ አንስተዋል፡፡

በአብነትም ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል አልፋ ወደ ጎረቤት ሀገራት መላክ መጀመሯም በውይይቱ ወቅት ተነስቷል፡፡

ፕሬዚዳንቷ በዚህ ወቅት እንዳሉት፥ እንደ አፍሪካ መሪዎች ሁላችንም በምግብ ምርት እራሳችንን ለመቻል ቆርጠን ተነስተናል ፤ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በስንዴ ምርት ራሷን ችላ ለጎረቤቶቿ ስንዴ ላኪ ሆናለች።

ይህ ስኬት እንዲመዘገብም በአፍሪካ ልማት ባንክ ቴክኖሎጅ ለአፍሪካ ግብርና ትራንስፎርሜሽን (ታት) አስተዋጽኦ ማድረጉ የተጠቀሰ ሲሆን ታት ሙቀትን የሚቋቋም የስንዴ ዘር ማሰራጨቱ ተጠቁሟል።

የአፍሪካ የምግብ እና የግብርና ንግድ በፈረንጆቹ 2030 በግምት 1 ትሪሊየን ዶላር እንደሚገመት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና (ዶ/ር) ለውይይቱ ተሳታፊዎች አብራተዋል።

ዝግጅቱ “ለውጡን መጠቀም ” በሚል መሪ ሃሳብ ዙሪያ ያጠነጠነ ነው፡፡

ከልዑካን እና ከተወያዮች ጋር አዳዲስ ሃሳቦችን በማሰስ ፈጠራን፣ ልዩነትን መፍጠር፣ የመቋቋም አቅምን ለማሻሻል የሚረዱ ዘዴዎችን፣ ከአደጋ ማገገም እንዲሁም የዓለም የምግብ ደህንነትን ለማረጋገጥ ዘላቂ ስርዓትን ስለመገንባት ሃሳቦች ተነስተዋል፡፡

በዚህ ወቅት ዓለም ላይ 65 በመቶ የሚሆነው መሬት ያልታረሰና ሆኖም ሊታረስ የሚገባው መሬት ያላት አህጉር እንደሆነች ተነስቷል፥ በዚህም አህጉሪቷ አብዛኛውን ጊዜ የምግብ ምርትን ከውጭ ታስገባለች፡፡

በዚህም የአፍሪካ መሪዎች ሀገራቸው በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ እና ምግብ ላኪ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥረት እያደረጉ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በፈርንጆቹ 2050 የዓለም ህዝብ ቁጥር ወደ 9 ቢሊየን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ ይህም በአፍሪካ እየጨመረ ያለውን የምግብ ፍላጎት ለማሟላት የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚገባ ነው የተገለጸው፡፡

34 የአፍሪካ መሪዎች የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና የአህጉሪቱን ሙሉ የግብርና አቅም በአምስት ዓመታት ውስጥ ለማሳካት በድርጊትና በውጤት ላይ ያተኮሩ እቅዶችን በማዘጋጀት የምግብና የግብርና አቅርቦት እንዴት እንደደግፉም አኪንዉሚ (ዶ/ር) አብራርተዋል።

ይህም በፈረንጆቹ 2016 ከጀመረው የባንኩ ‘ፊድ አፍሪካ ስትራቴጂ’ ዋና አካል ጋር የተጣጣመ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

አክለውም፥ ስትራቴጂው የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ከ250 ሚሊየን በላይ ሰዎችን ይደግፋል።

አጋሮች የምግብ ዋስትናቸውን ለመደገፍ ከ70 ቢሊየን ዶላር በላይ መውሰዳቸውን የተናገሩ ሲሆን፥ ባንኩ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 10 ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!