የሀገር ውስጥ ዜና

የፋይናንስ አቅርቦትን በማጠናከር የሕክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራ ነው – ሚኒስቴሩ

By Meseret Awoke

November 01, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት በጤናው ዘርፍ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ጥራት ያለው የሕክምና የአገልግሎት ተደራሽነትን ለማሣደግ በትኩረት እየሠራ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ለሦስት ቀናት የሚቆው 25ኛው የጤናው ዘርፍ ዓመታዊ ጉባዔ “ጠንካራ የጤና ፋይናንስ ቀጣይነት ላለው የጤና ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔው መጀመሪያ ቀን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እንዲሁም በሸገር ከተማ የሚገኙ የተለያዩ ጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ ጉብኝት ተደርጓል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማን ጨምሮ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የጤና ቢሮ ኃላፊዎች፣ የፌዴራል ተቋማት አመራሮችና በጤናው ዘርፍ አጋር ድርጅቶች÷ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኢሉ ወረዳ የሚገኘውን የቢሊ ጤና ኬላ ጎብኝተዋል።

እንዲሁም በሸገር ከተማ አስተዳደር የሰበታ ጤና ጣቢያና የማሕበረሰብ መድኃኒት ቤት አገልግሎት አሰጣጥን መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት÷ የጤና ዘርፍ ጉባዔ በጤናው ሴክተር የተከናወኑ ሥራዎችን ከተለያዩ የጤና ልማት አጋሮች፣ ከፌዴራልና ከክልል የጤና አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር የሚገመገምበትና አቅጣጫ የሚቀመጥበት ነው።

ጉባዔው የፋይናንስ ምንጮችን በመለየት በተለያዩ ሁኔታዎች የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ያለመ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የፋይናንስ አቅምን በማጎልበት ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የጤና መድን አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚደረግበት ሁኔታ ላይ ውይይት እንደሚካሄድም ነው ያመላከቱት፡፡

የውስጥ አቅምን ከማጎልበት በተጨማሪ አጋር ድርጅቶች ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ምክክር ይደረጋል ብለዋል፡፡

የጤና አገልግሎቱን ፍትሐዊነት ማረጋገጥና ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት በሚያስችሉ እንዲሁም የጤና ተቋማትን ግብዓት ችግር መፍታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ በመድረኩ ይመከራል ነው ያሉት፡፡

በዙፋን ካሳሁን

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!