አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር ዴዔታ ሰመሪታ ሰዋሰው በኢትዮጵያ ከቻይና ኤምባሲ የኢኮኖሚና ንግድ አማካሪ ሚኒስትር ያንግ ይሀንግ ጋር ውይይ ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
በውይይታቸውም የሁለቱ ሀገራት ቀጣይ የኢኮኖሚ ልማት ትብብር እና የልማት ድጋፍን በተመለከተ መምከራቸውን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
ያንግ ይሀንግ የልማት ድጋፍን በተመለከተ የቻይና መንግሥት 4 ነጥብ 1 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጣ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ እንደሚሰጥ አረጋግጠው ዝርዝር ፍላጎቱ በኢትዮጵያ በኩል እንዲቀርብ ጠይቀዋል።
ቻይና ለአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 21 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ የመለዋወጫ ዕቃዎች በዕርዳታ ለማቅረብ ቀደም ሲል በገባችው ቃል መሰረት አሁን 3 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ የመለዋወጫ ዕቃዎች አዲስ አበባ ደርሰው በርክክብ ሂደት ላይ መሆናቸውም ተገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታም ለአዲስ አበባ-ጂቡቲ ባቡር የሚያስፈልጉ የመለዋወጫ ዕቃዎች ግዥና አቅርቦት ይከናወናል መባሉን የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡
አረንጓዴ ልማትን የሚያበረታታ ኢንቨስትመንትን በተመለከተም የቻይና መንግሥት ኢትዮጵያን ጨምሮ ከ30 ሀገራት ጋር የመግባቢያ ሠነድ መፈረሙ የተመለከተ ሲሆን÷ በቀጣይ በቻይና በኩል በሚቀርብ ዝርዝር መርሐ- ግብር ከኢትዮጵያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተብራርቷል፡፡
የሁለቱ ሀገራት ኢኮኖሚያዊ ትብብር ሁሉ- አቀፍ ወደ ሆነ ያልተገደበ ትብብር መሸጋገሩ የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ይበልጥ መዋዕለ- ነዋያቸውን እንዲያፈሱ እንደሚያግዝ በውይይቱ ተነስቷል፡፡
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ መድረኮች የሁለቱን ሀገራት ጥቅም በሚጎዳ ጉዳዮች ላይ በጋራ እንዲታገሉና እንዲቆሙ የሚያስችላቸው ይሆናል ነው የተባለው፡፡
የተጀመረውን የብድር ክፍያ ማራዘሚያ ውይይት ለመቀጠልና ጉዳዩን በአጭር ጊዜ ለመቋጨት በሁለቱም ወገን ፍላጎት እንዳለ መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡