የሀገር ውስጥ ዜና

ትርክትን በማስተካከል ሂደት የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ዐሻራቸውን ሊያኖሩ ይገባል – ምሁራን

By ዮሐንስ ደርበው

November 02, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሕዝብ ተወካዮች እና አመራሮች ትርክትን በማስተካከል ሂደት ውስጥ ዐሻራቸውን ሊያስቀምጡ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

ባለፉት ዘመናት ኢትዮጵያውያን በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ትልቅ የትስስር ታሪክ ማስቀመጣቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥናት እና ምርምር ተቋም የአንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ደሳለኝ አምሳሉ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡

የፖለቲካችን አካሄድ በጥላቻ ትርክት ውስጥ መውደቁ፣ የማኅበራዊ መስተጋብር ዕሴቶች መላላት እና መሰል ችግሮች ለብሔራዊ ትርክት መዛባት መንስኤዎች ናቸው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ እስቴት ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የማኅበራዊ ሣይንስ መምህር ሬድዋን ዳውድ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ የግለሰብ፣ የሐይማኖት እና የብሔር ማንነታችንን ከሀገራዊ የጋራ ትርክቶቻችን ጋር አጣምረን ማስቀጠል ይገባል ነው ያሉት፡፡

በአርሲ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሣይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ጎሳ ሰጡ (ተ/ፕ)÷ ብሔራዊ ትርክት እና አንድነት ሲጎላ ጠንካራ እና ሉዓላዊነታችን የማይደፈር ሀገር ያደርገናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት ምሁራኑ÷ ፖለቲከኞች፣ ምሁራን፣ የሕዝብ ተወካዮች እና አመራሮች ትርክትን በማስተካከል ሂደት ውስጥ ዐሻራቸውን ሊያስቀምጡ እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

ሀገራዊ ትርክትን በማጉላት የኢትዮጵያን ሰላም፣ ዕድገት እና አንድነት ማፅናት እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በማርታ ጌታቸው