አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ ህብረት ከሰላም ስምምነቱ ባሻገር በናይሮቢ ፍኖተ ካርታ አፈፃፀም ላይ የተመዘገቡ ተግባራትን አድንቋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ለዘላቂ ሰላም ያደረጉት ስምምነት በዚህ ቀን እንደሆነ አስታውሰው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አንደኛ ዓመት መታሰቢያም የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት ላደረጉት ትብብር አመስግነዋል።
ሁለቱ አካላት ለከፈሉት መስዋዕትነት፣ ለማያወላውል ቁርጠኝነታቸው እና በትግራይ ክልል የጠብመንጃ ድምጽ እንዳይሰማ ላደረገው የጋራ ፖለቲካዊ ፍላጎታቸውም ነው ከሊቀ መንበሩ አድናቆት የተቸራቸው፡፡
የአፍሪካ ህብረት የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤትም ላሳየው አርዓያነት ያለው ሚና እና የአፍሪካ ባለድርሻ አካላት ለሰላም ስምምነት ላበረከቱት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ አክለውም፥ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች የአፍሪካ ህብረት አጋር ድርጅቶች ላደረጉት ተጨባጭ ድጋፍም አመስግነዋል።
ሊቀመንበሩ ከሰላም ስምምነቱ ባሻገር በናይሮቢ ፍኖተ ካርታ አፈፃፀም ላይ የተመዘገቡ ተግባራትንም አድንቀዋል።
በዚህም የከባድና መካከለኛ የጦር መሳሪያዎች ርክክብ፣ የመሠረታዊ አገልግሎቶች እድሳት፣ በትግራይ ክልል ትምህርት ቤቶችና የንግድ እንቅስቃሴዎች መጀመር፣ ጊዜያዊ ክልላዊ አስተዳደር እና የሽግግር ፍትህ ጉዳዮች ቡድን እንዲሁም መሰል ተግባራቶች መከናወናቸውንና መቋቋማቸው አንስተዋል፡፡
እነዚህ ወሳኝ ተግባራት በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላምና ደህንነትን ለማምጣት ሁለቱ አካላት ያሳዩት ቁርጠኝነትን እንደሚያመላክት ነው የገለጹት፡፡
የአፍሪካ ህብረት እየተገኙ ያሉትን ድሎች አጠናክሮ ለማስቀጠልና ያልተተገበሩ ጉዳዮችን በሰላም ስምምነቱ መሰረት እንዲፈቱ ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት አረጋግጠዋል።
ሊቀመንበሩ በትግራይ ክልል ይሁን በኢትዮጵያ እና በአጠቃላይ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሰላምን በጋራ መገንባት እና ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
#AU #Ethiopia #Tigray
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!