የሀገር ውስጥ ዜና

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ ገዱ  ከእንግሊዝ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተወያዩ

By Meseret Demissu

May 21, 2020

አዲስ አበባ፣ግንቦት 13፣2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸውከእንግሊዝ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ከሆኑት ጄምስ ፊሊፕ ደድሪጅ ጋር በቪዲዮ ኮንፈረንስ ተወያይተዋል።

ሁለቱ  ሚኒስትሮች በነበራቸው ውይይት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን በትብብር መግታት በሚቻልባቸው ጉዳዮች፣ በቀጠናዊ ጉዳዮች እና በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ትኩረት አድርገው መክረዋል ነው የተባለው።

በዚህም ወቅት አቶ ገዱ እንግሊዝ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ከኢትዮጵያ ጋር እያደረገች ላለው ትብብር እና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ሚኒስትሩ በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት በዓለም ላይ እና በተለይም በእንግሊዝ በደረሰው የበርካታ ሰዎች ሞት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

አቶ ገዱ  አያይዘውም ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንደሰፍን እያደረገች ያለውን አጠቃላይ እንቅስቃሴ   እና ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን እስከዛሬ ድረስ ያደረጉትን ውይይት በተመለከተም ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ከዚያም ባለፈ ሚኒስትሩ  ኢትዮጵያ የግድቡን ዉሃ የመጀመሪያ ሙሊት በቅርቡ እንደምታካሂድ እና በግብጽ በኩል የተያዘው የተሳሳተ አመለካከት በሶስቱ አገሮች በሚደረግ ውይይት እና ንግግር ሊፈታ የሚችል መሆኑን በማንሳት ዓለማቀፉ ማህበረሰብ ግብጽ ወደ ሶስትዮሽ ውይይት እንድትመለስ ጥረት ማድረግ እንዳለበት  ገልጸዋል።

ጄምስ ፊሊፕ ደድሪጅ በበኩላቸው÷ ኢትየጵያ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለምታደርገው እንቅስቀሴ እንግሊዝ ትብብሯንና ድጋፏን አጠናከራ እንደምትቀጥል  ጠቁመው÷የጤና ሚኒስቴር፣ የአፍሪካ በሽታዎች መቆጣጠረያ ማዕከል እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ የኮሮና በሽታ ስርጭትን ለመከላከል እያደረጉ ያለውን ጥረት አድንቀዋል።

አያይዘውም ኢትዮጵያ በቀጠናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን እያደረገች ያለውን እንቅሰቃሴም አድንቀው÷ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንበታ የውሃ ሙሊት ጋር በተያያዘ ሶስቱ አገሮች ልዩነታቸውን በውይይትና በድርድር እንዲፈቱ እንግሊዝ ድጋፏን እንደምታደረግ ሚኒስትሩ መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።