አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ የህገ መንግስት ትርጉምን በተመለከተ ያዘጋጀው የባለሙያዎች ሀሳብ መስጫ ተካሂዷል።
በዛሬው እለትም የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ከጤና ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረቡትን የባለሞያዎች ማብራሪያ ሰምቷል።
በውይይቱ ላይ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ሰብሳቢ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊን ጨምሮ ሌሎችም አባላት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊነት፣ ቫይረሱን የመከላከል እና የመቆጣጠር ምን ይመስላል እንዲሁም በሌሎች ከቫይረሱ ጋር የተያያዙ የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ እና የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኤባ አባተ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን አስመልክቶ እንዲሁም በተነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያም፥ በአሁኑ ወቅት በዓለም ዙሪያ 5 ሚሊየን ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን፣ 329 ሺህ ገደማ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን እንዲሁም ትናንት ብቻ በዓለም ዙሪያ 106 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን አንስተው፤ ይህም የቫይረሱ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ መሆኑን እንደሚያሳይ ጠቅሰዋል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሚተላለፍበት ዋነኛው መንገድም በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው መሆኑን በማንሳት፤ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ምልክቱን ማሳየት ከመጀመራቸው በፊት ወደ ሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚችል በመሆኑም ስርጭቱ አስቸጋሪ መሆኑን አንስተዋል።
በአሁኑ ወቅት ለቫይረሱ መድሃኒት ወይም ክትባት ባለመገኘቱ ከሰው ወደ ሰው እንዳይተላለፍ ማድረግ ብቸኛው መከላከያ መንገድ መሆኑንም ገልፀዋል።
ለዚህም አካላዊ ርቀትን መጠበቅን ጨምሮ አካላዊ ንክኪን ማስቀረት እና ሌሎች እርምጃዎችን መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን በመጥቀስ፤ ይህንን እና ሌሎችን የቫይረሱን መከላከያዎች ለመፈፀም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አስፈላጊ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ቫይረሱን የመከላከል እና የመቆጣጠርን አስመልክቶም ትምህርት ቤቶችን መዝጋት፣ የስራ ቦታ እና የትራንስፖርት ላይ መጨናነቅን መቀነስ ከውጭ የሚገቡትን ወደ ለይቶ ማቆያ ማስገባትን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ማወጅን ጨምሮ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውንም አንስተዋል።
በምርመራ መለየትን በተመከለተም ስራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን እና አንድ ተብሎ የተጀመረው ላቦራቶሪ አሁን ላይ 26 መድረሱን በላቦራቶሪዎቹም እስካሁን ለ65 ሺህ 760 ሰዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ለማድረግ መቻሉንም ዶክተር ሊያ ገልፀዋል።
በመቀጠልም የሕገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤው ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበውን የባለሙያዎች ማብራሪያ አድምጧል።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ ምርጫ ቦርድ ባስቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ምርጫን ለማድረግ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ ላይ ነበረ ብለዋል።
ሆኖም ግን የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ምርጫው መሰረዙን ያነሱት ሰብሳቢዋ፥ የምርጫ ሰሌዳውን ያሰረዘው ወረርሽኙ ብቻ ሳይሆን ወረርሽኙን ለመከላከል የተወሰዱ እርምጃዎች ናቸው።
በተለይም የስብሰባዎች መከልከል እና ትራንስፖርት ላይ የተጣሉ ገደቦችን እንደምሳሌ በመጥቀስ፥ እነዚህ ገደቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ቢነሱ ኖሮ በተጣበበ ጊዜም ቢሆን ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት እንደነበረም አብራርተዋል።
ሆኖም ግን ገደቦቹ በአጭር ጊዜ መነሳት ባለመቻላቸው ምርጫውን በተያዘለት ጊዜ ማካሄድ እንደማይቻል ማሳወቃቸውን ጠቅሰው፤ በዚህ ዙሪያም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር መደረጉን እና ይህንንም የተቀበሉ እና የተቃወሙ ፓርቲዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል።
ሰብሳቢዋ ወይዘሪት ብርቱኳን አክለውም፥ ቫይረሱ ለረጅም ጊዜ የሚቆይ ቢሆን እና ምርጫ መካሄድ አለበት ከተባለ ሁለት የቢሆን አማራጮች መዘጋጀታቸውን እና እነዚህም ከጤና ባለሙያዎች ጋር በቅርበት በመስራት የሚከናወን መሆኑን ገልፀዋል።
ይህንን ለማድረግም ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ምርጫውን ለማካሄድ እስከ 13 ወራት ጊዜ ሊወስድ እንደሚችልና ተጨማሪ ከ2 ነጥብ 5 ቢሊየን በላይ ብር ያስፈልጋል ያሉ ሲሆን፥ ይህም አጠቃላይ የቦርዱን ወጪ ከ8 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያደርሰው አስታውቀዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።