የሀገር ውስጥ ዜና

የሕዝብ ጥያቄዎችን ፈጥኖ በመፍታት ለግጭት የሚዳርጉ ክፍተቶችን መዝጋት ይገባል – የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

By Melaku Gedif

November 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች በወቅታዊ ሁኔታና በቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው።

በውይይት መድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ አጥነት ችግር የሰላም እጦት ምክንያት እየሆነ መምጣቱን ገልጸው÷ለወጣቶች የሥራ እድል መፍጠርና ሃብት እንዲያፈሩ ማድረግ ለግጭት ጊዜ እንዳይኖራቸው ያደርጋል ብለዋል።

በመንግሥት ተቋማት ላይ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ መፍትሔ ሊሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል።

እውነተኛ ሆነው ለሕዝብ ልማት ከሚሠሩት የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ይልቅ ከሚያማው ጋር የሚያሙና የሕዝብን ጥያቄ የማይመልሱ መበርከታቸውንም አንስተዋል።

የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች ለሕዝብ ልማት በሚጠቅሙ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርገው ሊሠሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት።

በመጀመሪያ ደረጃ በሕዝብና በመሪዎች መካከል መተማመን እንዲፈጠር መሥራት ይገባል ያሉት ነዋሪዎቹ፥ መሪዎችም በሕዝብ ዘንድ ታማኝ የሚያደርጋቸውን ሥራዎች መሥራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

የሕዝብ ጥያቄዎችን ሌሎች በመንጠቅ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጓቸው ስለመሆኑ በውይይቱ ላይ መነሳቱንም አሚኮ ዘግቧል፡፡

ነዋሪዎች ሕዝቡን ወደ ውዥንብር የሚያስገቡ መረጃዎችን ማጥራትና መመከት እንደሚገባ እና የመንገዶች መዘጋጋት የኑሮ ውድነቱን እያባባሰው መሆኑንም ጠቁመዋል።

የሀገርና የሰላም ጉዳይ ለነገ የሚባል እንዳልሆነ በማንሳትም ሀሰተኞችን መታገልና ሰላምን በጋራ ማጽናት ይገባል ነው ያሉት።

በከተማዋ በጦር መሳሪያ የታገዘ ቅሚያና ዘረፋ እየተስፋፋ መሆኑን ያነሱት ነዋሪዎቹ ሰላም እንፈልጋለን፤ በሀሰተኛ መረጃ ሀገር እና ሕዝብ ችግር ውስጥ እየገቡ መሆኑንም አውስተዋል።

“ሀሰተኛ መረጃ በማሰራጨት ሕዝብን ማጋጨት ሀገር የመሸጥን ያህል ነውር ነው” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የሕግ ማስከበር ሥራው በሕጋዊ መንገድ ብቻ መሠራት እንደሚገባውም ነዋሪዎቹ አመላክተዋል።

ለግጭት መነሻ የማይሆኑ ችግሮችን አጀንዳ አድርጎ ማንሳት የተገባ አይደለም፤ ትክክለኛ አጀንዳዎችን ግን በቁርጠኝነት መሥራት ይገባልም ብለዋል።

ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን መከላከል ከከተማ አሥተዳደሩ እንደሚጠበቅ ጠቅሰው÷ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሃሳቦች ላይ በስክነት መሥራት እንደሚገባም አስረድተዋል።

ከፖለቲካ መሪዎች በተጨማሪ የጸጥታ ሃይሎችም ከሕዝብ ጋር ጥልቅ ውይይት ማድረግ ይገባቸዋል ነው ያሉት።