የሀገር ውስጥ ዜና

ሰላምን ለማጽናት ሴቶችን ያማከለ ማህበረሰብ አቀፍ የምክክርና እርቀ ሰላም ስራዎችን መስራት ይገባል – አቶ አሻድሊ ሀሰን

By Shambel Mihret

November 03, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ሰላምን ለማጽናት የሴቶች ተሳትፎን ያማከለ ማህበረሰብ አቀፍ የምክክርና እርቀ ሰላም ስራዎችን መስራት ይገባል ሲሉ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻደሊ ሀሰን ገለጹ፡፡

የሴቶች ተሳትፎን ያማከለ ማህበረሰብ አቀፍ  የምክክርና እርቀ ሰላም ክልላዊ ፕሮጀክት ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብር ተካሄዷል፡፡

በአውሮፓ ህብረት የፋይናንስ ድጋፍ በቤርጎፍ ፋውንዴሽን እና በምክክር፣ የጥናትና ትብብር ማዕከል በጋራ እንደሚተገበርም ተገልጿል፡፡

የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አሁን የተገኘውን ሰላም ህዝባዊ መሰረት ማስያዝ እና ዘላቂነቱን ማረጋገጥ እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳደር አሻደሊ በመርሐ ግብሩ ላይ ተናግረዋል።

የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አሁን የተገኘውን ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የሰላም እጦት በዜጎች ህይወትና በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን ባለፉት አመታት በክልላችን ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር  ያጋጠመን ፈተና ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሴቶችን በማሳተፍ በህብረተሰቡ መካከል አንድነትንና አብሮነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት ጉዳይ አስፈፃሚ ዴቪድ ክሪቫንክ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ፕሮጀክቱ በክልሉ በመተከል ዞን በብዝሃ የአተገባበር ዘዴ የሚተገበር መሆኑን ተናግረዋል።

የአካባቢ ሰላም ግንባታ ኮሚቴ ጥምረቶችን አቅም በዘላቂነት መገንባት፣ የምክክርና የእርቀ ሰላም ተግባራትን መደገፍ፣ የግጭቶችን ስረ መሰረት በመለየት መፍትሄዎችን አመላክቶ በህብረተሰቡ መካከል አዎንታዊ ግንኙነትና አብሮነትን እንዲጠናከር ፕሮጀክቱ እንደሚሰራ መግለጻቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡