አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ የኮልፌ የግብርና ምርቶች የገበያ ማዕከልን ዛሬ መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አደረጉ።
ከንቲባዋ ባደረጉት ንግግር በአዲስ አበባ ሁሉም አቅጣጫዎች የሚገነቡ የገበያ ማእከላት የህዝቡን ኑሮ ለማቃለል አምራችና ሸማቹን ቀጥታ ማገናኘት መሆኑን ገልጸዋል።
ዋጋን ለማረጋጋት፣ ጥራቱን የጠበቀ ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ፣ የዋጋ ንረትን እየፈጠረ የሚገኘውን ህገወጥ ሰንሰለት ለመበጠስ ይረዳል ብለዋል።
የገበያ ማዕከሉ የሰብልና የአትክልት ማቆያና ማቀዝቀዣ ክፍል፣ችርቻሮ ክፍል፣ 200 የሚደርሱ መኪኖች ማቆሚያ እና መሰል ክፍሎች ያሉት ዘመናዊ የገበያ ማዕከል ነው።
በዘጠኝ ወራት ተሰርቶ የተጠናቀቀው ማዕከሉ የ24 ሰአት አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መሰራቱ ተገልጿል።
ማዕከሉ በመዲናዋ አራቱም አቅጣጫዎች የግብርና ምርቶች እንዲገቡ እና ተጠቃሚው ቀጥታ ከአርሶአደሩ ምርቶችን እንዲገዛ ታስበው እየተገነቡ ከሚገኙ ማዕከሎች ውስጥ አንዱ ነው።
ዛሬ የተመረቀውን የገበያ ማዕከል ጨምሮ በሌሎች ክፍለከተሞች እየተገነቡ የሚገኙት የገበያ ማዕከሎች የአርሶአደሩን ምርት ቀጥታ ለሸማቹ በማድረስ የከተማዋ የሚስተዋለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ያለመ ነው።
በተጨማሪም ትኩስ ምርቶችን ለሸማቹ ለማድረስ እንደሚጠቅም ተገልጿል።
በቅድስት አባተ