አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ከ5 ሺህ ለሚበልጡ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎችና በአካባቢው ለተጠለሉ ፍልሰተኞች ነፃ የዓይን ሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው።
ሕክምናው እየተሰጠ ያለው በዓለም አቀፍ የአረጋውያን አድን ድርጅት እና አርባ ምንጭ ሆስፒታል ትብብር ነው፡፡
ሕክምናው በነፃ መሰጠቱ የገንዘብ ዐቅም ለሌላቸው ሰዎች ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው የገለጹት ታካሚዎቹ÷ ከፍለው ለመታከም ዐቅም በማጣታቸው አጥተውት የነበረውን ብርሃን በማግኘታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡
ለረጅም ዓመታት ያስቸግራቸው የነበረው የዓይን ሞራ ግርዶሽ በቀዶ ሕክምና የተወገደላቸው መሆኑን የጋምቤላ ክልል ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል፡፡
የሕክምና ቡድኑ አስተባባሪ ዶክተር አሸብር ጤናው እንዳሉት÷ ድርጅቱ በዐቅም ማነስ ምክንያት ወደ ሕክምና ማዕከል ሄደው መታከም ለማይችሉ የዓይን ሕመም ላለባቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች አገልግሎቱን በአቅራቢያቸው እንዲያገኙ እየሠራ ነው።
በድርጅቱ አስተባባሪነት እየተሰጠ ያለው ሕክምና÷ የዓይን ሞራ ግርዶሽ፣ የዓይን ፀጉር ነቀላ፣ የዕይታ ችግር ላለባቸው መነፅር መስጠት፣ የዓይን ምርመራና ሕክምናን ያካተተ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ሕክምናው ከ5 ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች እንደሚሰጥ ጠቁመው÷ ከነዚህ መካከል 3 ሺህ የሚሆኑት የክልሉ ነዋሪዎች ሲሆኑ ቀሪዎቹ ፍልሰተኞች መሆናቸውን ነው የተናገሩት፡፡
በዘመቻው ላይ 12 የሕክምና ቡድኖች እየተሳተፉ እንደሚገኙም አስተባባሪው ገልፀዋል።