የሀገር ውስጥ ዜና

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በቀረበበት ተደራራቢ ክሶች ላይ የክስ መቃወሚያ አቀረበ

By Feven Bishaw

November 06, 2023

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም ባልቻ በቅፅል ስሙ (ልጅ ያሬድ) በተከሰሰባቸው ተደራራቢ ክሶች ላይ የክስ መቃወሚያ አቀረበ፡፡

ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) በዛሬው ቀጠሮ ከማረሚያ ቤት ቀርቧል።

የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ህግ በኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) ላይ ባቀረበበት በኮምፒዩተር የሚፈጸም ወንጀል ድንጋጌን መተላለፍ፣ የቤተክርስቲያንና የሰዎችን ክብርና መልካም ስም በማጉደፍ፣ ጥላቻ ንግግር ማሰራጨት የሚሉ ተደራራቢ ክሶች ማቅረቡ ይታወሳል።

የቀረበበትን ተደራራቢ ክስ በሚመለከት ኮሜዲያን ያሬድ ዘላለም (ልጅ ያሬድ) የክስ መቃወሚያውን በጽሁፍ አቅርቧል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የፀረ ሽብርና የህገመንግስት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በቀረበው የክስ መቃወሚያ ላይ ዐቃቤ ህግ መልስ እንዲያቀርብ ለህዳር 7 ቀን 2016 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ የማህበረሰቡን ክብርና ስነ-ልቦናን ከግምት ውስጥ በማስገባት የክሱ ዝርዝር ጉዳይ በሚዲያ እንዳይሰራጭ ችሎቱም በዝግ እንዲሆን ብይን መስጠቱ ይታወሳል።

በታሪክ አዱኛ