የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ ወደ ስራ መግባቱ ተመላከተ

By Mikias Ayele

November 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ “ብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂ” ፀድቆ ወደ ሥራ መግባቱን የፍትህ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አለምአንተ አግደው÷ ስትራተጂው የሕግ ድጋፍ ለማግኘት የገንዘብ አቅም የሌላቸዉ ዜጎች የመዳኘት መብት እንዲኖራቸው ያግዛል ብለዋል፡፡

አገልግሎቱ ባልተደራጀ መንገድ በፌዴራል እና በክልል የፍትህ ተቋማት እንዲሁም በግል ጠበቆች እና በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ስር በሚገኙ የሕግ ትምህርት ቤቶች ላይ ሲሲጥ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም በፍትህ ሚኒስቴር አዋጅ ቁጥር 1263/2014 እና በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(ሀ) መሰረት አግልግሎቱ ከጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲዉል መወሰኑን ገልፀዋል፡፡

ብሔራዊ ነጻ የሕግ ድጋፍ አገልግሎት ስትራቴጂውን ተግባራዊ ለማድረግም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በትብብር እንዲሰሩ ጥሪ ማቅረባቸውን የፍትህ ሚኒስቴር መረጃ ጠቁሟል፡፡