የሀገር ውስጥ ዜና

 አቶ ደመቀ መኮንን  ከተመድ የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ጋር ተወያዩ

By ዮሐንስ ደርበው

November 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ራሚዝ አላክባሮቭ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም በቀጣይ በሰብዓዊ እርዳታ እና ልማት ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው ሁኔታዎች ላይ መክረዋል፡፡

ራሚዝ አላክባሮቭ÷ ጽሕፈት ቤታቸው በቀጣይ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በሰብዓዊ እርዳታ እና ልማት ጉዳዮች ላይ በትብብር እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

አንድ ዓመት ባስቆጠረው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የተሠሩ ሥራዎችንም አንስተዋል፡፡

አቶደመቀ መኮንን በበኩላቸው ጽሕፈት ቤቱ በኢትዮጵያ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች አድንቀው÷ የተዘጋጀው ፍኖተ ካርታ አበረታች መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ከፕሪቶሪያው የሠላም ስምምነት ወዲህ በፌዴራል መንግስት የተከናወኑ ሥራዎችን  አስመልክተው ገለጻ አድርገዋል፡፡

በዚህም ከስምምነቱ ወዲህ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረቱን ፣ ሕወሓት ከሽብር ድርጊት ዝርዝር መሰረዙንና የፌዴራል መንግስት በጀት ለክልሉ መልቀቁን አስረድተዋል፡፡