የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያና ሕንድን የንግድ  ግንኙነት ማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

By Mikias Ayele

November 06, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ እና ሕንድን የንግድ ግንኙነት ማጠናከርና በመካከላቸው ያለውን የንግድ ሚዛን ማስተካከል የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል፡፡

በውይይቱ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ÷ኢትዮጵያ እና ሕንድ ረጅም ጊዜያትን ያስቆጠረ የንግድ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

የሕንድ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት፣በትምህርት ፣ በማኑፍክቸሪንግ፣ በጨርቃ ጨርቅ፣ በአግሮ ፕሮሰሲንግ፣ በቆዳና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ለሕንድ የሚቀርቡ ምርቶች መኖራቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ ÷ አሁን ላይ ያለውን የኢትዮጵያ እና ሕንድ የንግድ ግንኙነት በመገምገም  እና የገበያ እድሎችን በመለየት ሚዛናዊ የንግድና የኢኮኖሚ ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችሉ የመፍትሄ አቅጣጫዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመዋል፡፡

በሕንድ የኢኮኖሚ አማካሪና የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ልዑካን ቡድን ሰብሳቢ ፕሪያ ናይር በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ለሕንድ ባለሃብቶች ሁለተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት መዳረሻ ሀገር መሆኗን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የተመዘገቡ ከ650 በላይ የሕንድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ በሥራ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

መድረኩም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በመገምገም ያሉ ክፍተቶችን ላይ ለመምከር  ያለመ እንደሆነ ማስገንዘባቸውን የሚኒስቴሩ  መረጃ ያመላክታል፡፡