ዓለምአቀፋዊ ዜና

ተመድ የጁባ አካባቢ ነዋሪዎችን ከአካባቢያቸው በመልቀቅ ከጎርፍ አደጋ እንዲጠበቁ አሳሰበ

By Meseret Awoke

November 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት በጁባ እና ሸበሌ ወንዞች ላይ የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ መሆኑን አስጠንቅቆ መላው የጁባ አካባቢ ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲለቁ አሳሰበ።

በኬንያ እና ሶማሊያ የጣለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ በትንሹ 40 ሰዎች መሞታቸውን እና በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ መፈናቀላቸውን የእርዳታ ኤጀንሲዎች ገልጸዋል፡፡

በዚህ አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ቢያንስ የ25 ሰዎች ህይወት ከጠፋ በኋላ እና ቤቶች፣ መንገዶች እና ድልድዮች ከወደሙ በኋላ የሶማሊያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል።

በደቡብ ሶማሊያ ጁባላንድ ሉክ ግዛት በጎርፍ አደጋው ያሉበት ያልታወቁ 2 ሺህ 400 የሚገመቱ ነዋሪዎችን ለማግኘት የአደጋ ጊዜ እና የነፍስ አድን ሠራተኞች ጥረት እያደረጉ እንደሆነም ነው የተገለጸው።

በዚህም በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት በጁባ እና ሸበሌ ወንዞች ላይ የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ መሆኑን አስጠንቅቆ በመላው ጁባ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ከአካባቢው እንዲለቁ አሳስቧል።

የኤጀንሲው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሀሰን ኢሴ ለአሶሼትድ ፕሬስ እንደተናገሩት፥ የሶማሊያ አደጋ አስተዳደር ኤጀንሲ ለችግሩ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ወደ ዶሎው ሁለት ጀልባዎችን ከኪስማዮ ወደ ሉሉክ እና አንዱን ወደ ባራዴሬ ለማጓጓዝ እቅድ ተይዟል።

“በኢትዮጵያ ደጋማ ቦታዎች ላይ ተጨማሪ ውሃ መታየቱ አሁን እየደረሰ ያለው የጎርፍ መጠን በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ሊባባስ ይችላል” ሲሉም ነው የተናገሩት።

የጣለው ከባድ ዝናብ ሶማሊያን ለረሃብ አፋፍ የዳረጋትና ለአራት ተከታታይ አመታት የቆየውን ድርቅ ተከትሎ መሆኑንም ነው አውትሉክ የዘገበው።

የኬንያ ቀይ መስቀል በበኩሉ እንዳለው ፥ አርብ ከባድ ዝናብ መጣል ከጀመረ ወዲህ የሟቾች ቁጥር 15 መድረሱን የገለፀ ሲሆን፥ የወደብ ከተማ ሞምባሳ እና የሰሜን ምስራቅ ማንዴራ እና ዋጅር አውራጃዎች በከፋ ሁኔታ ተጎጂ ሆነዋል።

እስከ እሑድ ድረስ በደረሰ የጎርፍ አደጋ 241 ሄክታር የእርሻ መሬት አውድሟል፤ 1 ሺህ 67 የቤት እንስሳትን ገድሏልም ብሏል የኬንያ ቀይ መስቀል።

#Ethiopia #Somalia #Kenya

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!