የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌክትሮኒክ ግብይት ለሚገዙ እቃዎች የካርጎ ማዕከል ወደ ሥራ ሊያስገባ ነው

By Meseret Awoke

November 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016(ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በኤሌክትሮኒክ የግብይት ሥርዓት ለሚገዙ እቃዎች (ኢ-ኮሜርስ) የሚውል የካርጎ ማዕከል በቅርቡ ወደ ሥራ ሊያስገባ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ፥የካርጎ አገልግሎቱን ለማሳለጥ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሁለት ዘመናዊ የካርጎ ማከማቻና ማደራጃ ማዕከላትን ወደ ሥራ ማስገባቱን ጠቁመዋል።

ጎን ለጎንም 16 የጭነት አገልግሎት (ካርጎ) አውሮፕላኖች በሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የዘርፉን የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሳለጥ በመጪው ሰኞ ደግሞ 100 ቶን የመጫን አቅም ያለው ግዙፍ የካርጎ አውሮፕላን ከቦይንግ እንደሚረከብም ነው የገለጹት።

በተመሳሳይ በመጪዎቹ ሁለት ዓመታት ውስጥ አራት የካርጎ አውሮፕላኖችን አየር መንገዱ ተረክቦ ወደ ሥራ ለማስገባት እቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።

በተጓዳኝም ፥ አየር መንገዱ በ50 ሚሊየን ዶላር ያስገነባውን ሦስተኛውንና ለኢ-ኮሜርስ (በኦን ላይን ለሚገዙ እቃዎች) የሚውል ዘመናዊ የካርጎ ማዕከል በቅርቡ ወደ ሥራ ያስገባል ብለዋል።

ይህም በኤሌክትሮኒክ ግብይት ሥርዓት የሚገዙ እቃዎችን ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በአዲስ አበባ በኩል ለማጓጓዝና የገበያ ትስስሩን ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚያስችል መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአጠቃላይ ገቢው ከ30 እስከ 35 በመቶ የሚሰበሰበው ከካርጎ አገልግሎት መሆኑን ጠቁመው የዘርፉን አቅም ይበልጥ ለማጎልበት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

የአየር መንገዱ የጭነት አገልግሎት ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱንም ነው የገለጹት።

#Ethiopia #EthiopianAirlines #Cargo

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!