የሀገር ውስጥ ዜና

በሕገወጥ የፓስፖርት ሽያጭና ግዢ ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

By Shambel Mihret

November 07, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሕገወጥ የፓስፖርት ሽያጭና ግዢ ጋር ተያይዞ በድለላ ተግባር ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሌሎች 14 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።

ከትናንት ጀምሮ በቁጥጥር ስር የዋሉት ተጠርጣሪዎች በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ውስጥ ከሚሰሩ ሰራተኞች ጋር ከውጪ የፓስፖርት ገዢዎችን በማመቻቸትና በማገናኘት የሙስና የወንጀል ተግባር ተሳትፎ አላቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ናቸው ተብሏል።

ተጠርጣሪዎችን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ከብሔራዊ መረጃ ደህንነትና ከሌሎች የፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው ተገልጿል፡፡

እስካሁን ድረስ እነዚህን ጨምሮ በፓስፖርት ሕገወጥ ንግድ፣ ሰነድ አልባ ዜጎችን ወደውጭ በማስወጣትና በማስገባት ሕገወጥ የወንጀል ድርጊት የተጠረጠሩና በቁጥጥር ስር የዋሉ ተጠርጣሪዎች ቁጥር ከ60 በላይ ደርሷል።

ከፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው÷ በድለላ ተግባር ተሳትፈዋል ተብለው በቁጥጥር ስር የዋሉ 14 ተጠርጣሪዎች በነገው ዕለት ፍርድ ቤት ይቀርባሉ።

ሌሎች በሁለት መዝገብ በፍርድ ቤት ጉዳያቸው በጊዜ ቀጠሮ መዝገብ እየታዩ የሚገኙ 38 ተጠርጣሪዎች ጉዳይ ለተጨማሪ ምርመራ ለፖሊስ የ14 ቀን የምርመራ ማጣሪያ ጊዜ መሰጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በታሪክ አዱኛ