የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ

By Melaku Gedif

November 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ታምርት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ አስተባባሪ አቶ አያና ዘውዴ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት ÷ የውጪ ምንዛሪ እጥረት ለአምራች ኢንዱስትሪዎች ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኗል፡፡

ችግሩን ለመቀነስ እየተተገበረ ያለው ምርቶችን በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ ውጤት እያመጣ መሆኑን ጠቁመው፥ ለጸጥታ ሃይሎች የደንብ ልብስ በሀገር ውስጥ የመተካት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

ለአዲስ አበባ ተማሪዎች ለዩኒፎርም ብቻ ይወጣ የነበረ 37 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በሀገር ውስጥ በመተካት የውጪ ምንዛሪን ማስቀረት መቻሉንም አስረድተዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ስለሺ ለማ በበኩላቸው÷ ባለፉት ዓመታት ከውጭ ይመጡ የነበሩ አልባሳትን መተካት መቻሉን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይም ከ80 በመቶ በላይ አምራች ፋብሪካዎች በዚሁ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ነው የገለጹት።

በሃይማኖት ወንድይራድ