የሀገር ውስጥ ዜና

የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚፈቅድ ሕግ እየተዘጋጀ ነው ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

November 08, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የግል ባለሃብቶች በታዳሽ ኃይል ማመንጨትና ማሰራጨት ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚፈቅድ የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር እና ዓለም አቀፍ ሶላር አሊያንስ በኢትዮጵያ የፀሐይ ኃይል ልማትን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ምክክር ዛሬ በአዲስ አበባ አካሂደዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴዔታ ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንዳሉት÷ በ2022 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን ሙሉ በሙሉ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

በዕቅዱ መሰረት 65 በመቶው የሚሆነው የኃይል ፍላጎት ከብሔራዊ ግሪድ እንደሚቀርብ ገልጸው÷ 35 በመቶው ደግሞ ከዋና የኃይል ቋት ውጭ (ኦፍ ግሪድ) ይቀርባል ብለዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፀሐይ ብርሃን በአንድ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ በሰዓት 5 ነጥብ 5 ኪሎ ዋት ኃይልን የማመንጨት ዐቅም ቢኖርም እስካሁን ጥቅም ላይ የዋለው ከ400 ሜጋ ዋት እንደማይበልጥ ገልጸዋል፡፡

ለዚህም የግል አልሚዎች በዘርፉ ኢንቨስትመንት እንዲሰማሩ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩ አንዱ ምክንያት ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ለአብነትም “አንድ የግል ባለሃብት በዘርፉ ተሰማርቶ ከጸሃይ ብርሃን ኃይል በማመንጨት መሸጥ ቢፈልግ ክፍያ የሚጠይቅበት የሕግ ማዕቀፍ የለም” ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አቅርቦቱም ሆነ ስርጭቱ በመንግስት ብቻ መከናወኑ ዕድገቱን አዝጋሚ አድርጎት መቆየቱንም ነው ያነሱት፡፡

አሁን ላይ ይህን አሠራር በመቀየር የግል ባለሃብቱ ወደ ዘርፉ እንዲገባ የሚያስችሉ ፖሊሲዎች፣ አዋጆችና መመሪያዎችን ያጠቃለለ የሕግ ማዕቀፍ በመዘጋጀት ላይ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የዛሬው ምክክር ለህግ ማዕቀፎች ዝግጅት ግብዓቶችን ለማሰባሰብ ያለመ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

የዓለም አቀፉ ሶላር አሊያንስ ተወካይ ፍሬሕይወት ወልደሃና (ተ/ፕ) ጥምረቱ በአባል ሀገራት የፀሐይ ኃይል ልማት እንዲስፋፋ የሚሰራ መሆኑን አስገንዝበው÷ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የግል ባለሃብቱ በስፋት ወደ ዘርፉ እንዲገባ ለማድረግ በተለያዩ ስፍራዎች ለማሳያ የሚሆኑ ፕሮጀክቶችን እያከናወነና እየደገፈ እንደሚገኝም ነው የገለጹት፡፡