የሀገር ውስጥ ዜና

መንግሥት የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ ነው – አቶ ደመቀ መኮንን

By Feven Bishaw

November 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን መንግሥት የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ገለጹ፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ የአረጋውያን ቀን “የአረጋውያንን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር” በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርሐ ግብሮች በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።

ቀኑን አስመልክቶም አቶ ደመቀ መኮንን እና ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከልን ጎብኝተዋል።

በዚህ ወቅትም ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል ማዕከሉን በተጠናከረ መልኩ እንዲደግፍ አቶ ደመቀ ጥሪ አቅርበዋል።

መንግሥት የአረጋውያንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ፥ትውልዱ ለአረጋውያን ተገቢውን እንክብካቤና ድጋፍ በመስጠት መልካም ስብዕናቸውን መላበስ አለበት ብለዋል።

የመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል መስራችና ስራ አስኪያጅ ቢኒያም በለጠ በበኩላቸው ፥ ኢትዮጵያን ያገለገሉ ባለውለታ አረጋውያንን ማክበር ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

መንግስት፣ ተቋማትና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ለማዕከሉ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል።