የሀገር ውስጥ ዜና

የዓለም ባንክ ለሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ እድገት የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚያጠናክር አስታወቀ

By Meseret Awoke

November 09, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ ልዑካን ቡድን ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሴ እንዳሉት፥ ዘመናዊ የታክስ አስተዳደር ስርዓት በመገንባት ተቋሙ የያዘውን ሀገራዊ ወጪ በሀገራዊ ገቢ የመሸፈን ራዕይ ለማሳካት የዓለም ባንክ ድጋፍ አስተዋፅኦው የጎላ ነው፡፡

የዓለም ባንክ በሀገር አቀፍ ደረጃ እያደረገ ካለው የአጋርነት ድጋፍ አንዱ የገቢውን ዘርፍ መደገፍ መሆኑን የገቢዎች ሚኒስትር ዴኤታ ተስፋዬ ቱሉ ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ከፖሊሲ አንፃር፣ የታክስ መሰረትን ከማስፋት አኳያ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻል ብሎም ቴክኖሎጂን በማጠናከር ረገድ በቀጣይ በስፋት ድጋፍ እንደሚያደርግ መናገራቸውን ከሚኒሰቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

የዓለም ባንክ ልዑካን ቡድን ተወካይ ሚስተር ራጁል አዋስቲ ባቀረቡት ሰነድ እንደገለፁት፥ ከሀገር ውስጥ የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ በዋናነት የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከር በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ግብር ከፋይ ቁጥር ለማሳደግ የሚያስችሉ ድጋፎችን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

የዓለም ባንክ እያደረገ ያለው ድጋፍ የቴክኖሎጂ አቅምን በማጠናከርና ብቃት ያለው የሰው ኃይልን በመፍጠር ሚኒስቴሩ ከኢኮኖሚው ላይ የመነጨውን ገቢ በተሻለ አቅም ለመሰብሰብ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥርም ተመላክቷል፡፡

#Ethiopia #WorldBank

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-

ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!