የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ በተለዩ የትምሕርት መስኮች የውጭ ልምድ ያስፈልጋታል – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

November 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ በተለይም በተለዩ የትምሕርት መስኮች ላይ የውጭ ልምድ እንደሚያስፈልጋት የትምሕርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምሕርት ሚኒስትር እና የዩኔስኮ ብሔራዊ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ከተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት – ዓለም አቀፍ የትምሕርት ቢሮ (ዩኔስኮ- አይቢኢ) ቦርድ ፕሬዚዳንት ስቪን ኦስትቬት ጋር በፈረንሳይ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም÷ የኢትዮጵያን የትምሕርት ሥርዓት ለማሻሻል እና ለማዘመን የተከናወኑና በመተግበር ላይ ያሉ የለውጥ ተግባራትን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም በዘርፉ በተለዩ የትምሕርት መስኮች የውጭ ልምድ እንደሚያስፈልጋት በአጽንኦት መግለጻቸውን የትምሕርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

የዩኔስኮ-አይቢኢ የቦርድ ፕሬዚዳንት በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ የትምሕርት ሥርዓቱን በአዲስ መልክ ለማሻሻልና ለማዘመን የተከናወኑ ሥራዎችን አድንቀዋል፡፡

ቢሮውም የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡