የሀገር ውስጥ ዜና

ነዳጅን ከግብይት ስርዓት ውጭ በተገበያዩ ማደያዎች ላይ ዕገዳ ተጣለ

By Melaku Gedif

November 10, 2023

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ነዳጅን ከግብይት ስርዓት ውጭ በተገበያዩ ማደያዎች ላይ ዕገዳ መጣሉን የነዳጅ እና ኢነርጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

ከዲጂታል ነዳጅ ግብይት ስርዓት ውጪ ነዳጅን በመሸጣቸውና በስማቸው ከተጫነላቸው ነዳጅ በላይ በማደያቸው በሸጡ አዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች በሚገኙ 97 ማደያዎች ላይ የአንድ ወር እገዳ እና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ተገልጿል፡፡

ከዚህ ውስጥም 40 የነዳጅ ማደያዎች ላይ የአንድ ወር የነዳጅ ጭነት ዕገዳ የተጣለ ሲሆን፥ 57 ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዕገዳ የተጣለባቸው ማደያዎች ለባለስልጣኑ ከመስከረም10 እስከ ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም ባለው ጊዜ በደረሰው ሪፖርት መሠረት በስማቸው ከተጫነላቸው ነዳጅ በላይ መሸጣቸው ተጠቁሟል፡፡

የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ደግሞ ከተጫነላቸው ነዳጅ ከ50 እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ነዳጅ ብቻ በዲጂታል ግብይት መፈጸማቸው ተጠቅሷል፡፡

የነዳጅ ሕገ-ወጥ ንግድን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዲጂታል የነዳጅ ግብይት ሥርዓት ከሐምሌ 1 ቀን 2015 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ሸገር ከተሞች ተግባራዊ መደረግ መጀመሩ ይታወሳል፡፡