አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፈው ዓመት የኤሌክትሩክ ዘርፍ ከ12 በመቶ በላይ ዕድገት ማስመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
ከኢንዱስትሪ ዘርፍ አኳያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያና ምላሽም÷ በአጠቃላይ ባለፈው ዓመት የኢንዱስትሪ ዘርፉ 6 ነጥብ 9 ዕድገት ማስመዝገቡን ነው ያስታወሱት፡፡
ከዚህ ውስጥ የኤሌክትሪክ ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ መሆኑን በምላሻቸው አንስተዋል፡፡
የኮንስትራክሽን ዘርፍ 7 ነጥብ 1 እንዲሁም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍም 7 በመቶ ማደጉን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የገለጹት፡፡ ለኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ወሳኝ መሆኑን አንስተው÷ ኢትዮጵያ ታምርት በሚለው ንቅናቄ እንደሀገር የማምረት ዐቅማችን ያሉን ፋብሪካዎች ተደምረው 47 በመቶ ገደማ ነበር ብለዋል፡፡
ይህን አሃዝ አሁን ወደ 55 በመቶ ማሣደግ መቻሉን አረጋግጠው÷ የተገኘው ውጤት አበረታች ቢሆንም ተጠናክረው መቀጠል ያሉባቸው ጉዳዮች እንዳሉም አመላክተዋል፡፡
እንዲሁም ÷ የጨርቃ-ጨርቅ ዘርፍ 63፣ የቆዳ ዘርፍ 58፣ የቴክኖሎጂ ዘርፍ 35፣ የኬሚካል ዘርፍ የማምረት ዐቅም 68 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
ተኪ ምርቶችን በተመለከተም ከነበረው 30 በመቶ የማምረት ዐቅም አሁን ላይ 38 በመቶ መድረሱን አብራርተዋል፡፡
ተኪ ምርቶች ላይ በትጋት መሥራት በመቻላችን እንደ ድንጋይ ከሰል እና የቢራ ገብስ ያሉ ምርቶችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ መተካት ተችሏል ብለዋል፡፡
በዮሐንስ ደርበው