የሀገር ውስጥ ዜና

ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ብቸኛ መተንፈሻዋ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

By ዮሐንስ ደርበው

November 14, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቀይ ባህር የኢትዮጵያ ብቸኛ መተንፈሻዋ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደብን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ እንዳሉት ፥ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በአፍሪካ ቀንድ ያሉ ሀገራት እንዲሁም መላው የአፍሪካ ሀገራት፣ የምዕራብና የምስራቁ ዓለም ሀገራት እንዲገነዘቡ የምንፈልገው ይህ የኢትዮጵያ እውነተኛ ፍላጎትና ችግር ነው፡፡

የዛሬ 30 ዓመት ገደማ ኢትዮጵያ የሁለት ወደብ ባለቤት እንደነበረች አስታውሰው ፥ የሕዝብ ብዛቷም 46/47 ሚሊየን ገደማ ሕዝብ እንደነበራትና ከ12 እስከ 13 ቢሊየን ዶላር ገደማ ጠቅላላ የሀገር ውስ ገቢ እንደነበራት ጠቁመዋል፡፡

ከ30 ዓመት በኋላ ግን ከሁለት ወደብ ባለቤትነት ወደቦችን በንግድ ሕግ ወደምትጠቀምበት ደረጃ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰዋል፡፡

አሰብን እና ጅቡቲን በገንዘቧ፣ በንግድ ሕግ፣ በስምምነት ወደመጠቀም ዝቅ ማለቷንም አንስተዋል፡፡

ከተወሰነ ጊዜ በኋላም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ግጭት ሲያጋጥም ከሁለት ወደብ አንድ ወደብ ብቻ ወደመጠቀም ዝቅ ማለቷን ገልጸዋል፡፡

ቀይ ባሕር ያስፈልገናል የማይል የዓለም ክፍል እንደሌለ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ይህን ጥያቄ ኢትዮጵያ ስታነሳው ነውር መሆን እንደሌለበት አጽንዖት ሰጥተው ገልጸዋል፡፡

የወደብ ጉዳይን አዲስ ጥያቄ አድርገው የሚያነሱ እንዳሉ በማውሳትም የጎረቤት ሀገራትን ሉዓላዊነት ለመጉዳት የተነሳ አስመስለው የሚያቀርቡ እንዳሉም ነው ያብራሩት።

ነገር ግን ኢትዮጵያ የማንንም ሀገር ሉዓላዊነት የመጉዳትና የመውረር ፍላጎት የእንደሌላትም አስረድተዋል።

ለአብነትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የተገነባው ማንንም ለመጉዳት ሣይሆን ራስን ጠቅሞ ሌሎች ጎረቤት ሀገራትን ለማገዝም እንደሆነ ማወቅና መረዳት እንደሚያስፈልግም ነው የገለጹት፡፡

እንደሕዳሴ ግድቡ ሁሉ ቀይ ባሕርንም እንደዚሁ ለመጠቀም እንደሆነ መረዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ያልተገባ ጥያቄ ከህግ ውጪ አልጠየቀችም፤ ወደ ጎረቤት ሀገራት አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎትም የላትም ፤ ነገር ግን በህግና በቢዝነስ ማዕቀፍ እንወያይ” ነው ያልነው ብለዋል፡፡

ወንድም ሀገራት ለኢትዮጵያ ብቻ ብለው ሣይሆን ችግሩ ከመጣ ወደሀገራቸው ይዞ የሚመጣውን መዘዝ በመገንዘብ የኢትዮጵያን ጥያቄ ማድመጥና መፍትሄ ማበጀት እንደሚገባቸው አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ይሕን ለማድረግ ግጭት እንደማትፈልግ በማውሳትም ግጭት እንዳይመጣ በመነጋገር ችግሮቻችንን አብረን በመፍታት በጋራ እንደግ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የዓለም መንግስታትም 120 ሚሊየን ሕዝብ ለርሀብ፣ ለችግር፣ ለመበተን እንዳይጋለጥ መፍትሄ እንዲያገኝ ማገዝ አለባቸውም ነው ያሉት።

ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ለጊዜው ሊመስል ይችላል እንጂ አያዋጣም ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

በዚህ ጉዳይም ሁሉም በቀና ልብ ተባባሪ እንዲሆን አደራም ብለዋል፡፡

በመሰረት አወቀ