አዲስ አበባ፣ ሕዳር 4፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ የተመራ ልካን ቡድን እስከ አርብ በሚካሄደው የዱባይ የአየር ትርዒትና አውደ ርዕይ ላይ እየተሳተፈ ነው፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ መሳሪያ አምራች ተቋምት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዛሬው ዕለትም ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የመከላከያ ኢታማዦር ሹም ሌተናል ጀነራል ዒሳ አል ማዙሪ ጋር በሁለቱ እህትማማች ሀገራት መካከል ስላለው ወታደራዊ ጉዳዮች ትብብር ላይ መክረዋል፡፡
እንዲሁም የኢፌዲሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳም በአየር ትርዒቱ ላይ የተሳተፉ ሲሆን ÷ ከጉብኝታቸው ጎን ለጎን በኤይሮ ስፔስ ዘርፍ የካበተ ልምድ ያላቸውን ተቋማትና የሥራ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል፡፡
በተጨማሪ ትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ(ዶ/ር) እና የተለያዩ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በትርዒቱ ላይ እየተሳተፉ ነው::
በየሁለት ዓመቱ በሚካሄደው የዱባይ አየር ትርዒት እና አውደ ርዕይ ዘመናዊ የአየር ቴክኖሎጂዎችን ለዕይታና ለገበያ እንደሚቀርቡ ከአቡዳቢ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡