የሀገር ውስጥ ዜና

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

By ዮሐንስ ደርበው

November 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በጋራ ለመሥራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ።

የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አድማሱ ዳምጠው እንደገለጹት÷ የመግባቢያ ሠነዱ በዩኒቨርሲቲው በኩል የሚከናወኑ የመማር ማስተማር አገልግሎት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች፣ የማኅበረሰብ አቀፍ የልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፡፡

በስምምነቱ መሠረት የተለያዩ የሚዲያና የኮሙኒኬሽን ሥራዎች በፋና ዲጂታል ሚዲያ፣ በፋና ቴሌቪዥን እና በፋና ሬዲዮ ተዘጋጅተው የሚሠራጩ ይሆናል፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ዩኒቨርሲቲው ራስ ገዝ ሆኖ በተደራጀበት በዚህ ወቅት በርካታ ሐሳቦች እና እውቀቶች በሚንሸራሸሩበት ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር መሥራታችን ትልቅ ምዕራፍ ነው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በዩኒቨርሲቲው የሚሰጡ ጋዜጣዊ መግለጫዎች፣ የምርምር ሥራዎች፣ ማኅበረሰብ አቀፍ አገልግሎቶች እንዲሁም የተማሪዎች ምረቃ ፕሮግራሞች እና ሌሎችም ጉዳዮች ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር እንደሚሠሩም ነው ያስታወቁት፡፡

በሌላ በኩል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሚዲያው በዩኒቨርሲቲው በሚሸፍናቸው ሥራዎች ዩኒቨርሲቲው በገንዘብ የሚደግፍ ይሆናል ነው የተባለው፡፡

በተጨማሪም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚሰጣቸውን የትምህርት ዕድሎች በአገልግሎት ልውውጥ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የሚያቀርብ መሆኑም ተመላክቷል፡፡

በቅድስት ተስፋዬ

#Ethiopia

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!