የሀገር ውስጥ ዜና

የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የምርጫ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ ነው – የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር

By Melaku Gedif

November 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የሎጂስቲክስ አቅም ለማሳደግና የወደብ ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የባህር በር መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ገለጸ።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዴዔታ ደንጌ ቦሩ÷ ኢትዮጵያ 40 ምርጥ የሎጂስቲክስ አገልግሎት ካላቸው ሀገራት ተርታ እንድትመደብ ለማድረግ ሀገራዊ የሎጂስቲክስ ስትራቴጂ ተዘጋጅቶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሒደት በተከናወኑ ተግባራት የሀገሪቱን የሎጂስቲክስ ሥርዓት በማዘመንና በማሻሻል ረገድ አበረታች ውጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።

በዘርፉ የተለያዩ የማሻሻያ ሥራዎች ቢከናወኑም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት የሎጂስቲክስ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በመሆኑም የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የሎጂስቲክስ አቅምን ለማሳደግና በወደብ አገልግሎት እየገጠማት ያለውን ችግር በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የባህር በር የሌላቸው ሀገራት የእድገት ምጣኔያቸው 20 በመቶ ወደ ኋላ ይጓተታል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የዘርፉን እድገት የሚያፋጥን መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም የሀገሪቱን አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት እድገት ከ25 እስከ 30 በመቶ ማሳደግ ስለሚያስችል መሠረታዊ ጥያቄ መሆኑን አብራርተዋል።

የወደብ አገልግሎት ክፍያ በየዓመቱ እየጨመረ መሆኑን ጠቅሰው÷ ይህም ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት ብቻ 1 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ማውጣቷን አስታውሰው÷ ከዚህ በላይ የሚባክኑ በርካታ ነገሮች እንዳሉ አስረድተዋል።

በመሆኑም ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት መሥራት ይገባል ያሉት አቶ ደንጌ÷ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ የምርጫ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።