የሀገር ውስጥ ዜና

በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን በመከተል የጦር መሳሪያ ዝውውርን ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባ ተገለጸ

By Mikias Ayele

November 15, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የጦር መሣሪያ ዝውውር አዋጅን ተግባራዊ በማድረግና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን በመከተል የጦር መሳሪያ ዝውውርን ሥርዓት ማስያዝ እንደሚገባ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ተናገሩ፡፡

በፌዴራል ፖሊስ ዋናው መሥሪያ ቤት የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር ወርክሾፕ ዛሬ ተካሂዷል፡፡

መድረኩ በጦር መሳሪያ ምልክት አደራረግ ስልት፣ ደህንነትና አያያዝ፣ በዓለም አቀፍ የቀላል ጦር መሣሪያ ቁጥጥር ስታንደርድ፣ በቀላል የጦር መሣሪያዎች ጥገናና አወጋገድ ሂደት እንዲሁም በጦር መሳሪያዎች ክትትልና ልየታ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተመላክቷል።

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በወቅቱ እንደተናገሩት÷ የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ሽብርተኝነትና ህገ-ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በስፋት የሚስተዋልበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍም መንግሥት የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን የጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ወደ ስራ እንዲገባ ማድረጉን አስታውሰዋል።

በመንግስት እጅ ያሉ የጦር መሣሪያዎች ለህገ-ወጦች ተላልፈው እንዳይሰጡ ለመከላከል የጦር መሳሪያ ምልክት ማድረጊያ ማሽኖች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ለባለሙያዎች ስልጠና መሰጠቱን አስታውሰዋል፡፡

አክለውም ባለድርሻ አካላት የጦር መሳሪያ አስተዳደር ቁጥጥርን ለማጠናከር የሚያስችል ስራ መስራት አለባቸው ሲሉ ማሳሰባቸውን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡