አዲስ አበባ፣ ሕዳር 5፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር አብዲ መሐመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)ን ጨምሮ 10 ተከሳሾች በዛሬው ዕለት የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት ጀምረዋል፡፡
የሰው መከላከያ ማስረጃ ማሰማት የጀመሩት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የፀረ- ሽብርና የሕገ- መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።
የፍትሕ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሾቹ ላይ ጥር 22 ቀን 2011 ዓ.ም ባቀረበው የክስ ዝርዝር ላይ እንደተመላከተው÷ በ2010 ሰኔና ሐምሌ ወራት ባሉት ቀናት በሶማሌ ክልል አንዱ በሌላው ላይ የጦር መሣሪያ እንዲያነሳና የእርስ በርስ ግጭት እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ ”ሄጎ” በሚል ስያሜ የሚታወቁ ወጣቶችን ማደራጀት የሚል ይገኝበታል።
በተከሰተው ግጭት ምክንያትም÷ የ59 ሰዎች ሕይወት አልፏል፣ 266 ሰዎች ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸውል፣ 412 ሚሊየን ብር የሚጠጋ የመንግሥትና የግል ንብረት ወድሟል፣ የሐይማኖት ተቋማት ተቃጥለዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ በርካታ የከተማው ነዋሪዎችም ተፈናቅለዋል በማለት ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ተሳትፎ ደረጃ ጠቅሶ ተደራራቢ ክስ ማቅረቡ ይታወሳል።
ተከሳሾቹም በጊዜው የክስ ዝርዝሩ ከደረሳቸው በኋላ ወንጀሉን አልፈጸምንም ብለው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተዋል።
ፍርድ ቤቱም ዐቃቤ ሕግ ካስመዘገባቸው ከ213 ምስክሮች መካከል የ81 ምስክሮችን ቃል በተለያየ ቀንና ወራት አዳምጧል።
የምስክር ቃል የመረመረው ፍርድ ቤቱ የሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አብዲ መሐመድ ኡመር፣ የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሐት ጣሂር፣ የበርከሌ ዞን የቀድሞው ፖሊስ አዛዥ አብዱላሃ አሕመድ ኑርን ጨምሮ 26 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቶ ነበር፡፡
ከነዚህ ተከሳሾች መካከልም÷ 3ኛ፣ 5ኛ፣ 7ኛ፣ 11ኛ እና 18ኛ ተከሳሾች የቀረበባቸው የክስ ድንጋጌ አንቀጹ ተቀይሮ በአንቀጽ 239 እና በአንቀጽ 257 መሰረት እንዲከላከሉ ነበር ብይን የተሰጠው።
በአጠቃላይ ተከላከሉ ከተባሉት 26 ተከሳሾች መካከል 16ቱ በሌሉበት ነው እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠው።
በዚሁ መዝገብ የተካተቱ ሌሎች 9 ተከሳሾች በሌሉበት፣ 7 ተከሳሾች ደግሞ ከማረሚያ ቤት በቀረቡበት ጊዜ መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ ፍርድ ቤቱ ብይን መስጠቱም ይታወቃል፡፡
እንዲከላከሉ ብይን የተሰጠባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙት የሶማሌ ክልል የቀድሞው ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አብዲ መሐመድ ኡመር፣ የሶማሌ ክልል የቀድሞው ፖሊስ ኮሚሽነር ፈርሐት ጣሂር እና የበርከሌ ዞን የቀድሞው ፖሊስ አዛዥ አብዱላሃ አሕመድን ጨምሮ 10 ተከሳሾች የመከላከያ ማስረጃ ማሰማት ጀምረዋል።
በዚሁ መሠረት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር ካሏቸው የሰው ምስክሮች መካከል ዛሬ አምስት የሰው የመከላከያ ማስረጃዎችን አቅርበዋል።
በታሪክ አዱኛ
#Ethiopia
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡- ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/ ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/ ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡ ኢንስታግራም፦ https://www.instagram.com/fana_television/ ቲክቶክ፦ https://www.tiktok.com/@fana_television
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!