አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ገብተው በተለያዩ የሙያ መስኮች ስልጠና የሚወስዱ ተማሪዎች የመግቢያ ነጥብ ይፋ አድርጓል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል÷ ዜጎች ወደ ቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚመጡት መሄጃ ስላጡ ሳይሆን ያላቸውን እምቅ አቅም አውጥተው መጠቀም እንዲችሉ ነው ብለዋል፡፡
ይህም የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለዜጎች ዕድል ፈጣሪ አቅሞች እና ተጨማሪ አማራጭ የሚሰጡ ተቋማት ያደርጋቸዋል ነው ያሉት፡፡
ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው አዲሱ የትምህርትና ሥልጠና ፖሊሲ መሰረት ከዚህ ቀደም እስከ ደረጃ 5 ብቻ ተገድቦ የነበረው የቴክኒክና ሙያ ስልጠና የእድገት መሰላል እስከ ደረጃ 8 ድረስ እዲሆን መደረጉ ጠቁመዋል፡፡
ይህም ፖሊሲው ደረጃ ስድስትን ከመጀመሪያ ዲግሪ፣ ደረጃ ሰባትን ከማስተርስ እንዲሁም ደረጃ ስምንትን ከዶክትሬት ዲግሪ ትይዩ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም በዚህ ዓመት የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ነጥብ ያመጡ ተማሪዎች ወደ ቴክኒክና ሙያ መግባት ቢፈልጉ በደረጃ 6 ገብተው መሰልጠን እንደሚያስችላቸው አመላክተዋል፡፡
ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረጃ 6 የቴክኒክና ሙያ ሰልጣኞች እንደሚስተናገዱ ጠቁመው÷ በዚህ ዓመት በተቀመጠው መስፈርት መሰረት በክልሎች አማካኝነት የሰልጣኞች ምደባ ይካሄዳል ብለዋል፡፡
በዚህም በተያዘው የሥልጠና ዘመን 632 ሺህ በላይ ተማሪዎች የሥራ ገበያውን የሰው ሃይል ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ከደረጃ 1 እስከ ደረጃ 5 እንደ ውጤታቸው ተመድበው እንደሚሰለጥኑም ጠቅሰዋል፡፡
በወጣው መቁረጫ ነጥብ መሰረት ደረጃ አንድ እና ሁለት 110 ሺህ 15 ፣ በደረጃ ሦሰት እና አራት 412 ሺህ 557 እንዲሁም በደረጃ አምስት 110 ሺህ 15 ሰልጣኞች እንደሚሳተፉ አንስተዋል፡፡
በደረጃ ስድስት ደግሞ 2 ሺህ የሚሆኑ ሰልጣኞችን ለቀመበል ዝግጅት እንደተደረገ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የ2016 የስልጠና ዘመን የተዘጋጀው መቁረጫ ነጥብ የ2015 ትምህርት እና የ2014 ዓ.ም የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ማጠቃለያ ፈተና የወሰዱ ተማሪዎች ላይ ተግባራዊ ይሆናልም ብለዋል፡፡
ከ2014 ዓ.ም በፊት ለነበሩ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ደግሞ በስልጠና ዘመኑ በነበረው መቁረጫ ነጥብ መሰረት እንደሚስተናገዱ ተጠቁሟል፡፡
የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በ2016 ዓ.ም ቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ያዘጋጀው የመግቢያ ነጥብ ከዚህ በታች ባለው ሰንጠረዥ ቀርቧል፡-