አዲስ አበባ፣ ህዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለም አቀፍ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክና የቅርስ ማዕከል መቀመጫውን በኢትዮጵያ አድርጎ እንደሚመሰረት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ማዕከሉ ሕዳር 28 ቀን 2016 መቀመጫውን በኢትዮጵያ አድርጎ ሲመሰረት ቀደም ብሎ ሰፊ የዲፕሎማሲ ስራ መከናወኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል።
የዚህ ማዕከል በኢትዮጵያ መቀመጫውን ማድረግ በዲፕሎማሲም ሆነ በኢኮኖሚ ረገድ ሰፊ እድል ይዞ እንደሚመጣም ተናግረዋል፡፡
ማዕከሉ የጥቁር ህዝቦችን ታሪክና ቅርስ የተመለከቱ ሰፊ የምርምርና የጥናት ስራዎች እንደሚካተትበት ተገልጿል።
ኢትዮጵያ የዚህ ማዕከል መቀመጫ ሆና ስትመረጥ ለጥቁር ህዝቦች ታሪክና ነጻነት ቀድማ በሰራችውና እየሰራች ባለችው ተግባር፣ የሰው ልጆች መገኛና በቅኝ ግዛት ያልተገዛች ሐገር መሆኗ አበይት የመመረጫ ምክንያቶች መሆናቸው ተመልክቷል።
ሕዳር 28 ቀን 2016 ዓ.ም ምስረታውን በሚያደርገው የጥቁር ህዝቦች ማዕከል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች በተገኙበት እንደሚከፈት ተመላክቷል፡፡
በፍሬሕይወት ሰፊው