የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ሙክታር ከድር ከባፍሎ ከተማ ከንቲባ ጋር ተወያዩ

By Shambel Mihret

November 16, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 6፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሙክታር ከድር (ዶ/ር) ከባፉሎ ከተማ ከንቲባ ፕሪንሰስ ፋኩ እና ሌሎች አመራሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ የኢስትለንደን ኢትዮጵያዊን ማህበረሰብ ማህበር አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱ በዋናነት በሁለትዮሽ ጉዳዮች፣ በህዝብ ለህዝብ ትብብሮች፣በአካባቢ ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እና በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

አምባሳደ ሙክታር÷የኢትዮጵያእና የደቡብ አፍሪካ ግንኙነት ታሪካዊና በጠንካራ የወንድማማችነት መሰረት ላይ የተገነባ እንደሆነ አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ህዝቦችና ለአፍሪካ ሀገራት የነጻነት ትግል በተለይም በደቡብ አፍሪካ የጸረ አፓርታይድ የነጻነት ትግል ወቅት ኔልሰን ማንዶላን ጨምሮ ለትግሉ መሪዎች ቀጥተኛ ድጋፍ በማድረግ ታሪካዊ ሚና የነበራት መሆኑን አጠቅሰዋል፡፡

የሁለትዮሽ ግንኙነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጎለበተ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅትም በሁሉም የትብብር ዘርፎች ስትራቴጂካዊ ግንኙነት ደረጃ ላይ እንደደረሰ መናገራቸውን የኤምባሲው መረጃ ያመላክታል፡፡

በባፍሎ ከተማና አካባቢው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከመስተዳድሩና ከሚመለከታቸው የመስተዳድሩ አስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየተቀሳቀሱ እንደሚገኙ በመጠቆም የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

አፍሪካዊ ወንድማማችነት ይበልጥ እንዲጠናከር ኤምባሲውና የማህበረሰቡ አመራሮች ከከተማ መስተዳደሩ ጋር ትብብራቸውን አጠናክሮ ለማስቀጠል ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል፡፡

የባፋሎ ከተማ ከንቲባ ፕሪንሰስ ፋኩ በበኩላቸው÷ አምባሳደርና ልዑካቸው በከተማው በመገኘት በሁለቱ ሀገራት ታሪካዊ ግንኙነት፣ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና በአካባቢው ስለሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ዙሪያ በትብብር ለመስራት ላሳዩት ፍላጎት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በስራ ታታሪነታቸው፣ በመልካም ስነምግባራቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብና መስተዳድሩ ጋር በመልካም መስተጋብርና ትብብር እንደሚንቀሳቀሱ ተናግረዋል፡፡

በተለይም ወንጀልን ጨምሮ በቢዝነስ ሥራቸው ላይ እያጋጠሙ ያሉትን ተግዳሮቶች በጋራ ለመቅረፍ የሚያስችሉ ለሌሎች አካባቢዎች ምሳሌ ሊሆን የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸዋል፡፡

ኤምባሲው፣ መስተዳድሩና የአካባቢው የኢትዮጵያዊን ማህበረሰብ አባላት ያላቸውን ሁለንተናዊ ትብብር አጠናክረው ለማስቀጠል መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተጠቁሟል፡፡