የሀገር ውስጥ ዜና

በሀገራዊ ምክክሩ ዙሪያ ከዳያስፖራዎች ጋር ውይይት እየተካሄደ ነው

By Feven Bishaw

November 18, 2023

 

አዲስ አበባ ፣ ሕዳር 8 ፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሚናና ተሳትፎ ለአገራዊ ምክክርና ለአገራዊ መግባባት” በሚል መሪ ኃሳብ ከዳያስፖራ አባላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በዚሁ ጊዜ እንዳሉት÷ ኮሚሽኑ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅትና የተሳታፊዎች ልየታ ጨምሮ ሌሎች ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

ሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የዳያስፖራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ዳያስፖራው በምክክሩ ተሳትፎ ማጠናከር አለበት ብለዋል።

በምክክሩ ሂደቱ ዳያስፖራው የበኩሉን ተሳትፎ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆን ዳያስፖራው ባለው እውቀት የኮሚሽኑን ሥራ ሊደግፍ እንደሚገባ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ዳያስፖራው የሀገራዊ ምክክሩ ሥራ እንዲሳካ ተሳትፎውን እንደሚያጠናክር የገለጹት ደግሞ ዳያስፖራውን በመወከል ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ዳያስፖራ ማኅበር አባል ካፒቴን ሰለሞን ግዛው ናቸው።

በምንችለው ሁሉ የሀገሪቱ ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ ዳያስፖራው እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የበኩሉን እንደሚወጣም ገልጸዋል።