የሀገር ውስጥ ዜና

በሶማሌ ክልል የሕብተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

By Shambel Mihret

November 18, 2023

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 8፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሶማሌ ክልል በሕብረተሰቡ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ገለጸ፡፡

በፌዴሬሽን ምክር ቤት አስተባባሪነትና በሶማሌ ክልል አስተናጋጅነት በጅግጅጋ ከተማ የሚከበረው 18ኛው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓልን አስመልክቶ የጋዜጠኞች ቡድን በክልሉ የተገነቡ የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው፡፡

የሶማሌ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ፈርሀን ጅብሪል በወቅቱ፥ በሕብረተሰቡ ላይ ተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች እየተገነቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በፀጥታው ረገድም ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው÷ ከዚህ በፊት የፀጥታ ስጋት የነበረባቸው አካባቢዎች አሁን ላይ አስተማማኝ ሰላም ሰፍኖባቸዋል ብለዋል፡፡

የ18ኛውን የብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበርም የቅድመ-ዝግጅት ሥራዎች እየተጠናቀቁ እንደሚገኙም አስታውቀዋል፡፡

የቀብሪ ደሀር ከተማ ከንቲባ አብዱራዛቅ አወል በበኩላቸው÷ በከተማው የሕብተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከተማዋ ከልማት እንቅስቃሴ ርቃ እንደነበር አስታውሰው÷ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሁለንተናዊ ዘርፍ መነቃቃት ተፈጥሯል ብለዋል።

የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታን ጨምሮ የሕብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋልም ነው ያሉት።

በዚህም የዜጎችን ደህንነት ከመጠበቅ በላይ የንግድና የኢንቨስትመንት መነቃቃቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሉንም አንስተዋል።

የዘንድሮው የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በዓል ከኅዳር 25 እስከ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ “ብዝኃነትና እኩልነት ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡

በወንድሙ አዱኛ